አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካን የበረራ መስመር እንደሚቀይር ተስፋ የተጣለበትን ግዙፍ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየገነባች መሆኗን ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ በፈረንጆቹ 2030 ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ይህ አቅሙ ወደ 110 ሚሊየን መንገደኞች ከፍ እንደሚል የጠቀሰው ዘገባው፥ በዚህም በዓለማችን በርካታ መንገደኞችን በማስተናገድ ቀዳሚ ከሆነው አትላንታ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚበልጥ አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንገደኞች በአፍሪካ ውስጥ የአውሮፕላን ጉዞ ለማድረግ ከአህጉሪቱ ውጪ እንደ ዱባይ፣ ፓሪስ እና ለንደን የመሳሰሉ ከተሞችን ትራንዚት ለማድረግ እንደሚገደዱ ሲኤንኤን በዘገባው ጠቅሷል፡፡
ነገር ግን በ12 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ባሳለፍነው ጥር ወር ግንባታው የተጀመረው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይህንን ችግር በማስቀረት ለአህጉሪቱ አዲስ የበረራ መስመር እንደሚያበጅ ተስፋ ተጥሎበታል ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአውሮፕላን ማረፊያውን ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት፥ ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ታሪክ ግዙፍ የአቪየሽን መሰረተ ልማት ነው ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፕሮጀክቱን 30 በመቶ ወጪ እንደሚሸፍን የአየር መንገዱን ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ የአቪዬሽን ገበያዎች አንዱ የሆነውን የአፍሪካን ሰማይ ለማገናኘት የሚደረገውን ውድድር እንዲመራ ያስችለዋል።
በተጨማሪም በዓመት 3 ነጥብ 73 ሚሊየን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም የሚኖረው ሲሆን፥ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በመደገፍ የአህጉሪቱን ጥቅም ላይ ያልዋለ የካርጎ አቅም ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።
የአፍሪካ አየር መንገዶች በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጭነት አገልግሎት እያስተናገዱ ሲሆን፥ ይህም በዓመት ከ15 እስከ 16 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ጠቁሟል፡፡
ፕሮጀክቱን በገንዘብ በመደገፍ ረገድ በተለይም እንደ አሜሪካ፣ ቻይና እና ጣሊያን ያሉ ሀገራት በሂደቱ እየተሳተፉ ሲሆን፥ በዚህም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ሲኤንኤን በዘገባው አመልክቷል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

