አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከሸገር ወደ ሀገር በሚል ርእስ የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የቱሪዝም ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የቱሪዝም ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፥ በአዲስ አበባ የተሰሩ ስራዎች ተምሳሌትነታቸው ወደ ሀገር የሚሻገሩ ናቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜ በመፈጸም እንዲሁም በተመደበ በጀት በመስራትና ለህብረተሰብ ጥቅም በዋማል ረገድ የነበሩ ችግሮችን የሚቀረፍ ጅምር ነው ብለዋል።
በአንድነት ፓርክ፣ በእንጦጦ እና በሸገር ፕሮጅክት የተያየው ውጤታማ ስራ እንደ ሀገር ከሀሳብ ማመንጨት ጀምሮ እስከ መፈፀም ያሉብንን ችግሮች ለመቅረፍ አዲስ ምእራፍ የከፈተ ሲሉም ተናግረዋል።
በሶስቱም ፕሮጀክቶች በአስተባባሪነት የሰሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ፥ ስራዎቹ የነበሩ ግን ያልተጠቀምንባቸውን ሀብቶች ማየት የቻልንበት ነው ብለዋል።
የመንግስት እና የግል አጋርነት ውጤታማነት የታየበት እንደሆነም ገልፀዋል።
እንደ ሀገር ለተጀመረው የብልፅግና ጉዞ ትልቅ ነገር አስቦ ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ የታየበት ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ ጊዜን፣ ጥራትን እና ዋጋን አጣጥሞ እንዴት ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው፥ ቱሪዝም በኢትዮጵያ የተጠበቀ ብቻ ሳይሆን የተደበቀ አቅም ከነበረበት የኢኮኖሚ መሰረት እንዲሆን ጅምር ውጤት የታዩባቸው ፕሮጀክቶች ናቸው ብለዋል።
ከቱሪዝም ተሻግሮም በሁሉም ዘርፍ እንደ ሀገር ያለን አቅም አውጥቶ የመጠቀም ልምድ የተያበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከአንድነት ፓርክ እስከ እንጦጦ ፕሮጀክት በስነ ጥበብ ስራዎች የተሳተፉት ወይዘሮ መስከረም አሰግድ፥ ስራዎቹ ሁሉ የስፍራዎቹን ተፈጥሮ ሳይረብሹ መሰራታቸውን ተናግረዋል።
ሀገር ወዳድ በጎ ፍቃደኛ ዜጎች ሳይሰስቱ ለኢትዮጵያ ሙሉ እውቀታቸውን የሰጡበት እንደሆነም ገልፀዋል።
በአላዛር ታደለ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

