አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ውስብስብ የቆዳ በሽታዎችን እና ካንሰርን ቀድሞ መለየት እና ማከም የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል አሉ፡፡
5ኛው የአፍሪካ የቆዳና የአባላዘር ህክምና ማህበር ጉባኤ ተካሄዷል፡፡
ሚኒስትሯ በጉባኤው ላይ እንዳሉት÷ የቆዳ ህክምናን ከመሰረታዊ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ጋር በማዋሃድ ተደራሽነቱን ለማስፋት ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው።
የቆዳና የአባላዘር በሽታን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በመከላከል ላይ ብቻ ያተኩር የነበረው ፖሊሲ አሁን ላይ መከላከልን እና ህክምናን አጣምሮ በያዘ መልኩ መሻሻሉን አንስተዋል።
የቆዳ በሽታ ከተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ጋር በቀጥታ የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ውስብስብ የሆኑ የቆዳ በሽታዎችን እና ካንሰርን ቀድሞ መለየት እና ማከም የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።
የህክምና ቅብብሎሽ ስርዓቱን በማሻሻል አገልግሎቱን ለተጋላጭ እና ርቀት ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የዲጂታል ጤና ቴክኖሎጂዎች ይበልጥ ትክክለኛ እና አፍሪካዊ እውነታን ያገናዘቡ እንዲሆኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓቶችን በአፍሪካውያን መረጃ እና ተሞክሮ ማበልጸግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ400 በላይ የህክምና ባለሙያዎች በሀገር ውስጥ በተለያዩ የልዩ ሙያ ዘርፎች ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የቆዳና አባላዘር ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ሽመልስ ንጉሴ÷ አሁን ያለውን ዓለም አቀፍ የፖሊሲ ትኩረት በመጠቀም የቆዳ ህክምና አገልግሎትን በታችኛው የጤና መዋቅር እና በመሰረታዊ ጤና ጣቢያዎች ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአፍሪካ የቆዳና አባላዘር ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ቤን ሳሌም ሙአዝ በበኩላቸው÷ ጉባኤው የአፍሪካን የ”ደቡብ ለደቡብ” ትብብር እና የልምድ ልውውጥ ለማጠናከር ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
በዐምደወርቅ ሽባባው

