አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ኢራንን በጣሊያን መተካት እንደምትፈልግ ገለጸች፡፡
የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ፓውሎ ዛምፖሊ ፊፋ በዓለም ዋንጫው ኢራንን በጣሊያን እንዲተካ ጠይቀዋል።
ኢራን ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር በገባችበት ጦርነት ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የመካፈሉ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡
የኢራን ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ካለፉ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን÷ ጣሊያን ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ከውድድር ውጪ መሆኗ ይታወሳል፡፡
የአራት ጊዜ የመድረኩ አሸናፊዋ ጣሊያን ከ2026 ዓለም ዋንጫ ውድድር ውጪ መሆኗን ተከትሎ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ከኃላፊነት መነሳታቸው ይታወሳል፡፡
የጣሊያን መንግሥት በበኩሉ÷ ሀገሪቱ ኢራንን እንድትተካ የቀረበውን ሐሳብ በይፋ ተቃውሟል።
የጣሊያን ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሉቺያኖ ቦንፊግልዮ እንዳሉት÷ ጣሊያን በመጪው የዓለም ዋንጫ ውድድር ኢራንን የመተካት ፍላጎት የላትም፡፡
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በችሎታ እና በጠንካራ ስራ መሆን አለበት በማለት ሐሳቡን ውድቅ አድርገዋል፡፡
የጣሊያን ስፖርት ሚኒስትር አንድሪያ አቦዲ በበኩላቸው÷ የቀረበው ሐሳብ አስፈላጊ አይደለም፤ ሜዳ ላይ አሸንፈን ነው ማለፍ ያለብን ብለዋል።
የጣሊያን የገንዘብ ሚኒስትር ጂያንካርሎ ጆርጅቲ ሐሳቡ አሳፋሪ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህ መንገድ ወደ ዓለም ዋንጫ ከሄድን ያሳፍራል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ፊፋ በበኩሉ÷ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ የሚያዘጋጁት የ2026 ዓለም ዋንጫ ውድድር በታቀደው ፕሮግራም እንደሚቀጥል ማሳወቁን የቲ አር ቲ ዘገባ አመላክቷል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ

