Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቀጣዩ ዓመት ከ20 ነጥብ 3 ጊጋዋት በላይ የሶላር ኃይል ይመረታል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ ሀገር በሚቀጥለው ዓመት ከ20 ነጥብ 3 ጊጋዋት በላይ የሶላር ኃይል ይመረታል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ የቶዮ ሶላር ኢነርጂ ሁለተኛው ምዕራፍ፣ ኦርጅን እና ሉሚንቴክ የሶላር ፋብሪካዎች እንዲሁም የኤች.ዜድ ጋዝ ፋብሪካዎችን በዛሬው እለት መርቀው ከፍተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከጥቂት ዓመታት በፊት ፓርኩ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ይመረትበት እንደነበርና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) ስትወጣ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች ለቀው በመውጣታቸው 90 በመቶ ባዶ እንደነበር አስታውሰዋል።

በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማገናዘብ ለኢትዮጵያ በአንድ ዘርፍ ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ጉዞ እንደማያዋጣ መረዳት በመቻሉ ወደ ቬትናም በማቅናት ልምዶችን በመውሰድ ለኢንቨስተሮች ግብዣ መቅረቡን ጠቅሰዋል።

ከቬትናም ጉብኝት በኋላ ያየነውን ዘመናዊ ፋብሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማየት ጓግተን ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቶዮ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ ከጀመረ በኋላ የመጀመሪያውን ዙር 2 ጊጋዋት ሶላር በማምረትና ሌላ 4 ጊጋ ዋት መጨመሩን እንዲሁም ሌሎች ሁለት ኩባንያዎች ደግሞ ሶላር ማምረት የጀመሩበትን ሂደት አንስተዋል።

በመቀጠልም ዛሬ የተመረቁት ሶስት የሶላር ፋብሪካዎች 11 ነጥብ 3 ጊጋዋት የሶላር ኃይል ማምረት የሚችሉ እንደሆኑ ገልጸው፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ በሐዋሳ ብቻ 15 ነጥብ 3 ጊጋዋት የሶላር ኃይል እንደሚመረት ጠቁመዋል።

እንዲሁም በደብረብርሃን 3 ጊጋዋት፣ በአዲስ አበባ 2 ጊጋዋት የሶላር ኃይል ማምረት መጀመሩን ጠቅሰው፤ በድምሩ እንደ ሀገር በሚቀጥለው ዓመት ከ20 ነጥብ 3 ጊጋዋት በላይ የሶላርሃይል እንደሚመረት አስገንዝበዋል።

እነዚህ ፋብሪካዎች ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለሀገር የሚያስገኙ እንደሆኑ አስረድተዋል።

በፋብሪካዎቹ ውስጥ ከሞላ ጎደል አብዛኛው ስራ የሚሰራው በሮቦት፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በአጠቃላይ በቴክኖሎጂ በመታገዝ እንደሆነም አብራርተዋል።

ይህንን ቴክኖሎጂ የመጠቀም ልምምድ ማሳደግ ከታቻለ በአጭር ጊዜ ብዙ ምርት የሚያመርቱና ትልቅ ሃብት የሚያስገኙ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ መቀላቀል እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት።

በሶስና አለማየሁ

Exit mobile version