Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ግንባታና የአፍሪካ አቪየሽን ልህቀት ተምሳሌት ነው – ከፍተኛ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገር ግንባታ ጉልህ ሚናው ብሔራዊ ኩራትን ከመፍጠር ባለፈ የአፍሪካ አቪየሽን የልህቀት ተምሳሌት ነው አሉ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት በማስመልከት ከደንበኞችና አጋሮች ጋር የደንበኞች ተሞክሮ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የአየር መንገዱን አገልግሎት በተመለከተ በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
አሕመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የላቀ ውጤት ያለውና ለረጅም ዓመታት ስኬትን ማስቀጠል ያስቻለ ግዙፍ የመንግሥት የንግድ ኩባንያ ነው።
አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታና በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማህበራዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ያለው ተቋም ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ አየር መንገዱ የሀገር ኩራት የሆነ ሁሉም የኔ የሚለው የጋራ ማንነት መገለጫ ብሔራዊ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ በዘርፉ የመቻልና የልህቀት ማሳያ የሆነ ተቋም መሆኑን አንስተው፥ የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
ለአገልግሎት ዘርፍ ኤክስፖርት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው ፥ ለንግድ መሳለጥና ለሥራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ÷ አየር መንገዱ ግዙፍ የሎጅስቲክስ መሠረተ ልማት አቅም መገንባቱን ገልጸው፥ ለወጪ ንግድ እንዲሁም ለዲፕሎማሲ ትልቅ ሚና ያለው ተቋም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገን ዛሬ እየገነባ የሚገኝ አኩሪ ኩባንያ እንደሆነ ማውሳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
Exit mobile version