Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኤ አይ የሰውን ልጅ የፈጠራ አቅም የሚያሰፋ እንጂ የሚተካ አይደለም – ነብዩ ባዬ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) የሰውን ልጅ የፈጠራ አቅም የሚያሰፋ እንጂ የሚተካ አይደለም አሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና ከእሑድ ኤ አይ ስቱዲዮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) የሙዚቃ ውድድር ተካሂዷል፡፡

ነብዩ ባዬ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ÷አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ጥርጣሬ እና ስጋት ይገጥማቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ እውቀትንና ፈጠራን የሚጠቀሙ በመሆናቸው መሰል ተግዳሮቶችን በማለፍ አሁን ያለበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ መድረስ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ዛሬም የሰው ሰራሽ አስተውሎት በጤና፣ ግብርናና በሌሎች ዘርፎች ሲጀመር ተመሳሳይ ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም አሁን ላይ በርካታ ውጤቶች ማግኘት እየተቻለ መሆኑን አብራርተዋል።

በለውጡ መንግሥት የተቋቋመው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ሀገሪቱ ከዓለም ጋር እኩል እንድትራመድ እያደረገ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ሙዚቃና ጥበብ የሰው ልጅ የምናብ ውጤቶች እንደሆኑ እና የኮምፒውተር ሳይንስ ደግሞ ለሙዚቃ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ዛሬ ላይ ተወዳዳሪ ወጣቶቹ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በጥበብ ዘርፍ ማሽንና ሰው ተቀናጅተው መስራት እንደሚችሉ ማሳየት ችለዋል ነው ያሉት፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ የፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች ራሳቸውን እንዲገልጹ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም የቴክኖሎጂ ሜዳን በማስፋት የፈጠራ አቅምን እንደሚያጎለብት አስረድተዋል፡፡

በሙዚቃው ዘርፍ አዲሱን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ አቀናጅቶ በሚገባ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለውድድሩ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉት ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ለእሑድ ኤ አይ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትር ዴዔታው መሰል ሥራዎች በፊልም እና በሌሎች የጥበብ ዘርፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version