አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የጋራ ማንነትን የሚገነቡና ለሀገራዊ ግቦች በቁርጠኝነት የሚሰሩ መሆን አለባቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት “የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በለውጡ ዓመታት በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ በተደረገው ሪፎርም የሚታይ ለውጥ ተመዝግቧል።
የለውጡ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አቅምን ለማሳደግና ነፃና ገለልተኛ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን ለመፍጠር በሙያቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችን መፍታት የመጀመሪያው ርምጃ እንደነበር አስታውሰዋል።
በሙያቸው ምክንያት ተዘግተው የቆዩና ወደ ሀገር ቤት ገብተው እንዳይሠሩ የተከለከሉ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ወደ ሀገራቸው መጥተው እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸዋል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ በመገናኛ ብዙኃን ሪፎርሙ ከውጭ ሆነው የሚዘግቡ መገናኛ ብዙሃን ይጠለፉ (ጃም ይደረጉ) የነበረበትን አሠራር ማስቀረት እንደተቻለ ጠቁመው÷ በለውጡ መንግሥት የፀረ-ሽብር አዋጁን ጨምሮ ሌሎች አሳሪ ሕጎች ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል ብለዋል።
ይሁን እንጂ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ሲከፈት ወደ ሙያው ለመግባት የተቸገሩና ነፃነታቸውን ማስተዳደር ያልቻሉ ባለሙያዎች በመፈጠራቸው ለዘርፉ ፈተና እንደሆኑ ገልጸዋል።
በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ባይፈቱም መልካም ሥራዎች ተከናውነዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ያዩትንና የሰሙትን እውነት የሚዘግቡ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የጋራ ማንነትን የሚገነቡ መሆን እንዳለባቸው ገልጸው÷ መገናኛ ብዙሃን በቅንጅት ለማወያየት የበለጠ ክፍት መሆን እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የሌሎችም ዘርፎች ዋልታ ረገጥነት ቀርቶ ሚዛናዊነት መንገስ እንዳለበትም አሳስበዋል።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በቂ ጥላቻ፣ መናናቅና መከፋፈል ተዘርቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ አሁን መገናኛ ብዙሃን በአንድነትና የተሳሳቱ ትርክቶችን ማቅናት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙኃን የዘገባ ዓላማን፣ አተያይን፣ ሙያዊ ብቃትን እንዲሁም ቅርበትን መሠረት አድርገው መሥራት ይገባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

