Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሚዲያን ለጋራ ትርክት …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎”የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በሚዲያ ዘርፍና ተቋማት ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች ላይ የሚመክር መድረክ ትናንት ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ካጋሩት ሀሳብ መካከል፤ በሆነ ጊዜ ሰዎች አንድን ዘውግ አጉልተው ሊሆን ይችላል፤ ይህ ደግሞ እንደማይጠቅመን አይተናል የሚለው ነው።

በመሆኑም የአንድ ዘውግ መጉላትን ተከትሎ የመጣውን ብልሹ አሰራር እና ልምምድ ማስፋት ጎጂ መሆኑን በማስገንዘብ፤ በሚያሰባስበን እና አንድ በሚያደርገን ጉዳይ ላይ ማተኮር ይበልጥ ለጉዟችን የተመቸ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።

ለዚህ ደግሞ ከህትመት ሚዲያ እስከ ማህበራዊ ሚዲያ ድረስ ያሉት ተቋማት ባለፉት ዓመታት ለአሰባሳቢ የጋራ ትርክት የሰጡትን ትኩረት አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በማህበረሰብ ውስጥ መረጃን ለማስተላለፍ፣ ህዝብን ለማስተማር እና አመለካከትን ለመቅረጽ ከፍተኛ ሚና ያለው ሚዲያ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብዝሃ ብሔር፣ ቋንቋ እና ባህል ላላቸው ሀገራት ቁልፍ ሚና አላቸው።

ሚዲያው ማህበረሰቡን ለማቀራረብ፣ የጋራ እሴቶችን ለማጎልበት እና ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ከባድ የቤት ስራ ያለበት በመሆኑ በትጋት መስራት ይጠበቅበታል።

እንደ ሰላም፣ አንድነት፣ መቻቻል፣ ፍትህ እና መከባበር ያሉ እሴቶችን ለጋራ ማንነት መገንቢያ መሳሪያ አድርጎ ለመጠቀም የተሳሳተ መረጃ እና የጥላቻ ንግግርን መከላከል ላይ በጥንቃቄ መስራት ይገባል።

ሚዲያው እውነተኛ፣ ሚዛናዊ እና ተጠያቂ መረጃ በማቅረብ የህዝብ እምነትን ማጠናከር ያለበት ሲሆን፤ በዚያው ልክ ፍትሐዊ የህዝብን ተሳትፎ ማረጋገጥ የግድ ይለዋል።

ይህም ሚዲያው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ እንዲሰማ እድል በመስጠት በሀገር ጉዳይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል ይኖርበታል።

ሚዲያው የሃሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የውይይት መድረክ የመፍጠር እና የፖለቲካ የማህበራዊ እና የባህል ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ የመፍጠር ሚናም ይወጣል።

በተጨማሪም የአንድ ሀገር የጋራ ትርክት በታሪክና በባህል ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ሚዲያው የተለያዩ ባህሎችን እና ታሪካዊ ክስተቶችን በአዎንታዊ መንገድ በማቅረብ ህዝቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ የጋራ ትርክት እና አብሮነት እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ሚዲያው ለጋራ ትርክት ግንባታ እንቅፋት የሚሆነውን አንድን ዘውግ ማጉላት ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል።

እንዲሁም የሐሰት ዜና፣ የጥላቻ ንግግር እና ሚዛናዊ ያልሆኑ ዘገባዎችን ከማቅረብ በመቆጠብ፤ የጋራ ትርክት በመገንባት የህዝብ የጋራ እሴቶችን በማጎልበትና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል የሚዲያው ዋና የቤት ስራው ነው።

በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version