አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ሊካሄድ ጥቂት ጊዜያት ለቀረው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ውድድር ፈተና ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመ።
ውድድሩን በሚያስተናግዱ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ያለው የአየር ንብረት በከፍተኛ ሙቀት፣ በነጎድጓዳማ ዝናብ እና በሰደድ እሳት የሚታወቅ መሆኑ ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ በርካቶችን እያሳሰበ ይገኛል።
በደቡባዊ አሜሪካ እና በሰሜናዊ ሜክሲኮ በሚገኙ ከተሞች ያለው አማካይ ከፍተኛ የቀን ሙቀት ከ30 እስከ 40 ዲግሪ ሴልሺየስ የሚደርስ ሲሆን÷ ይህም ለተጫዋቾች አስቸጋሪ እንደሚሆን ተመላክቷል።
ተጫዋቾች በውድድሩ ላይ ያላቸውን አቅም ለማሳየት ትልቅ እንቅፋት እንደሚሆንባቸውም ስጋት ፈጥሯል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ውድድር ላይ ስድስት ጨዋታዎች ተቋርጠው እንደነበር ይታወሳል።
በተጨማሪም ነጎድጓዳማ ዝናብ ለጨዋታዎች መቋረጥ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የተነገረ ሲሆን÷ በተለይ እንደ ማያሚ፣ ሂውስተን እና አትላንታ ያሉ ከተሞች ያላቸው የአየር ንብረት ለዚህ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
በዚህም ጨዋታ ከሚካሄድበት ስታዲየም በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት መብረቅ ከተከሰተ እንደ አሜሪካ መደበኛ አሰራር መሠረት መብረቁ ካቆመ በኋላም ለ30 ደቂቃ ጨዋታ ሊቋረጥ ይችላል።
ሌላኛው ፈተና በሰደድ እሳት ምክንያት የሚፈጠር የአየር መበከል ሲሆን÷ ከአሁኑ በአንዳንድ አካባቢዎች የሰደድ እሳት መከሰት መጀመሩ ተገልጿል።
ከዚህ በፊት በካናዳ በተከሰተ የሰደድ እሳት ጭሱ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዙ ምክንያት ጨዋታዎች እንዲሰረዙ መደረጋቸው ይታወሳል።
በእነዚህ ስጋቶች ምክንያት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን÷ በውድድሩ እያንዳንዱ ጨዋታ በሁለቱም አጋማሽ የ3 ደቂቃ የግዴታ ውሃ እረፍት እንዲደረግ ወስኗል።
በተጨማሪም አብዛኞቹ ጨዋታዎች ከሰዓት በኋላ ወይም ምሽት ላይ እንዲደረጉ መወሰኑ ተመላክቷል።
በሰደድ እሳት ምክንያት የአየር ጥራት ችግር ከተፈጠረ ደግሞ ወቅታዊ ሁኔታን እና የጤና ባለሙያዎችን ምክር ያገናዘበ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።
በዮናስ ጌትነት

