አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው የሕፃናትን ደኅንነት የሚያሻሽሉ ብሔራዊ መርሐ ግብሮች የትውልድ ግንባታ ዋስትና ናቸው አሉ።
የዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ÷ የቀዳማይ ልጅነት ልማት በሕግ እና በፖሊሲ ማዕቀፍ ተደግፎ እየተሰራ ነው።
መንግሥት ለሰው ተኮር ልማቶች ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ ሀገር አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ልማት እና የትምህርት የፖሊሲ ማዕቀፍ በ2003 ዓ.ም ጸድቆ በ2015 ዓ.ም ደግሞ ማሻሻያ ተደርጎበት በሥራ ላይ መዋሉን ለአብነት አንስተዋል።
ከዚህ ተጨማሪም በ2017 ዓ.ም የጸደቀው አጠቃላይ የትምህርት ዐዋጅ ነጻና አስገዳጅ የቅድመ አንደኛ ትምህርት እንዲሰጥ እንደሚደነግግ አስታውሰው፤ ይህንን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ ከ35 ሺህ በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በመንግሥት ተቋማትም የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግሥት ብልጽግናን ለማረጋገጥ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን በተደራጀ መልኩ በመላ ሀገሪቱ ለማስፋት ሙሉ ቁርጠኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአንድ በኩል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፤ በሌላ በኩል የተማሪዎችን የምገባ ስርዓት በማስፋፋት ልጆች በአካልና በመንፈስ የሚጎለብቱባቸው የስፖርትና የመዝናኛ ቦታዎች በየአካባቢው በመገንባት፤ በኮሪደር ልማት አማካኝነት ከተሞችና ሰፈሮች ለልጆች ምቹዎች እንዲሆኑ በማድረግ መንግሥት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ስርዓተ ምግብን በማሻሻል ተግባር በሰቆጣ ቃል ኪዳን አማካኝነት የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ከሁለት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን መቀንጨር በ2022 ዓ.ም ዜሮ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።
ከሰቆጣ ቃልኪዳን ጋር ተናባቢ በሆነ መልኩ በአምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ አልሚ ምግቦችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
በለይኩን ዓለም

