Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አፍሪካ በዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ በቂ ውክልና ሊኖራት ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋን በሚወስኑ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ በቂ ውክልና ሊኖራት ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በተገኙበት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ልዩ የቴምብር ስብስብ ይፋ ያደረገችበት መርሐ-ግብር ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የድርጅቱ የምሥረታ በዓል የባለ ብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ተቋማት ራሳቸውን ከሚለዋወጠው ዓለም ጋር እንዴት ማላመድ እንዳለባቸው የሚይሳይ ትልቅ አጋጣሚ ነው።

ከ80 ዓመታት በፊት ከአውዳሚው የዓለም ጦርነት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ሲመሰረት አባል የነበረችው ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ሥርዓት ጋር ያላት ታሪክ በመርህ ላይ የተመሰረተ እና በተለያዩ ፈተናዎች ያለፈ መሆኑን አውስተዋል።

ተቋማት ተቀባይነትና ሕጋዊነት የሚኖራቸው በሚፈተኑበት ወቅት ትክክለኛ ርምጃ መውሰድ ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ገልጸው፤ በባለብዙ ወገን ተቋማት ላይ የሚጣለው ተስፋ እና የሚጠበቅባቸው ኃላፊነትም እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።

በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት ይበልጥ ፍትሃዊ፣ ሁሉንም ያካተተ እና የዛሬውን የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ እንዲሆን መዋቅራዊ ለውጦችን ሊያደርግ ይገባዋል ብለዋል።

በተለይም አፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋን በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ድምፅ ሊኖራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አፍሪካ በዓለም አቀፍ ሥርዓቱ ውስጥ በቂ ውክልና ማግኘቷ የተቋሙን ተአማኒነትና ውጤታማነት እንደሚያጠናክረው አመልክተዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰላምና ጸጥታ፣ በልማት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በቴክኖሎጂ ዙሪያ በከፍተኛ ትኩረትና ፍጥነት መስራት እንደሚገባው ገልጸው፤ ይህም ትርጉም ያለው ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚፈልግ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ፍትሃዊና ውጤታማ በሆነ የዘርፈ ብዙ ትብብር እንደምታምንና ለወደፊትም በዓለም አቀፍ ሰላምና ልማት ግንባታ ላይ የበኩሏን ድርሻ መወጣቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም ለተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ላሳዩት ጽኑ ቁርጠኝነት እና ከአፍሪካ ጋር ላላቸው ቅን ግንኙነት አመስግነዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version