አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክሩ ተጨባጭ ውጤት ወደሚያስገኘው ቀጣይ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንን የእስካሁን ተግባራትና ቀጣይ አቅጣጫ የሚገመግም መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የምክክር ባህል እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በእስካሁኑ ሂደት በሀገሪቱ ሁሉም ማዕዘናት የሚገኙ ከ90 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያንን አመለካከቶችና የውይይት ውጤቶች ማንጸባረቁን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በማኅበረሰባችን በየደረጃው የመደማመጥን ከፍ ያለ ጠቀሜታ አሳይቷል ብለዋል፡፡
ያላሰለሰ የመነጋገር ልምምድና የሰከነ የወል መደማመጥ ለጠንካራ የሲቪክ ማኅበረሰብ ባህል ግንባታ መሰረታዊ ጉዳይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ይህ ወቅት ለሀገር ወሳኝ ፋይዳ የያዘው ምክክሩ ተጨባጭ ውጤት ወደሚያስገኘው ቀጣይ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት መሆኑን ጠቅሰው፥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለሀገራችን ሰላም፣ አንድነትና ዘላቂ መረጋጋትን የሚያረጋግጥ ገንቢ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት።
በትዕግስትና ከፍ ባለ የሙያ ስነምግባር የምክክር ሂደቱን ወደፊት በማራመድ አሁን ያለበት ምዕራፍ እንዲደርስ ላደረጉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

