Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለወጣቶቻችን የሥራ ዕድል ይከፍታል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

‎አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች ምቹ የንግድ ከባቢ ከመፍጠር ባሻገር በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶቻችን የሥራ ዕድል ይከፍታል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ‎የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ በዛሬው እለት መመረቁን ገልጸዋል፡፡

የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምዕራፍ አንድ ግንባታ መጠናቀቅ አስተማማኝ እና ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት በጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ተደማሪ እመርታ ነው ብለዋል፡፡

በመዲናችን በአጠቃላይ በ93 ነጥብ 9 ሄክታር መሬት ላይ ከሚያርፈው የፓርኩ ስፋት ውስጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ በ43 ሄክታር መሬት ላይ መገንባቱን አስታውቀዋል፡፡

ይህም ለመካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች ምቹ የንግድ ከባቢ ከመፍጠር ባሻገር በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶቻችን የሥራ ዕድል ይከፍታል ነው ያሉት።

‎ፓርኩ የሀገራችን አምራቾች አቅማቸውን በማጎልበት፣ ምርታማነታቸውን በማሳደግና ተወዳዳሪነታቸውን በመጨመር ለከተማችን፣ ለሀገራችንና ለቀጣናው የሚተርፉበት ታላቅ እድልን ይዟል ብለዋል።

በሌላ በኩል ተኪ ምርቶችን በማምረት በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ቀጥተኛና ቀልጣፋ የንግድ ትስስር ሲፈጥር፣ ምርቶችን ደግሞ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል ሲሉም ገልጸዋል።

Exit mobile version