አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአፍሪካ 10 ነጥብ 2 በመቶ እድገት የምታስመዘግብ ብቸኛ ሀገር ናት አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለውጥ የሚመጣው በስራ ብቻ በመሆኑ መትጋት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ብልጽግና በጋራ እናያለን ልጆቻችን በፍጹም አይለምኑም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እኔም እናንተም ካልሰራን ለውጥ አይመጣም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዓለም መጤ አይፈልግም፤ ስንከዳትም ስንመጣባትም ማትሰለቸው ኢትዮጵያ በመሆኗ ሀገራችንን መጠበቅና ማልማት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
በቱሪዝም ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ውጤት እያመጡ እንደሚገኙ ገልጸው፥ ሰዎች ከውጭ እየመጡ በልፋታችን የተገኘውን ውጤት እያደነቁ ባለበት ሁኔታ እኛ አላየንም ማለት የለብንም ብለዋል፡፡
በሰራነው ስራ ሌሎች በመደነቃቸው ሳንዘናጋ ይበልጥ የተሻለ ስራ ለመስራት መነሳሳት አለብን ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 10 ነጥብ 2 በመቶ እንደምታድግ ጠቅሰው፥ በድፍን አፍሪካ በዚህ ልክ የሚያድግ አንድም ሀገር የለም ነው ያሉት፡፡
ይህንን እድገት ይበልጥ በማፋጠንና በማስፋት ዜጎቻችንን መጥቀም አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መገፋፋት ስለማያዋጣ የእምነት፣ የቋንቋና የጾታ ልዩነቶችን ማክበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ከተከባበርንና አብረን መኖር ከቻልን ሀገራችን በጣም ውብ ለሁላችንም የምትበቃ ናት ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ጀምረን ያልጨረስነው እና አስበን ያላሳካነው አንዳች ነገር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የገንዘብ እጥረት፣ የሰዎች መለገምና የጊዜ ማነስ አልያዘንም ነው ያሉት፡፡
ሌብነት እንዳይኖርና ትጋት ከልብ እንዲሆን እንዲሁም ሁሉንም አቅፈን እንድንይዝና ልቦናችን ቀና እንዲሆን አደራ ማለት እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

