አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መረጃ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነባበት ቁልፍ የሉዓላዊነት ምሰሶና የዚህ ዘመን ስትራቴጂያዊ ሀብት ነው አሉ።
”የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በሚል መሪ ሀሳብ ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ባስመዘገበችው ስኬት ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገጻች ባሰፈሩት መልዕክት፥ በዘርፉ የተመዘገበው ድል በተበሰረበት ሀገራዊ ጉባኤና ኤግዚቢሽን ላይ ተገኝቼ የተመለከትኩት እመርታ እጅግ አስደሳች ነው ብለዋል።
በውጭ አካላት ላይ ጥገኛ የሆነ መረጃ ሀገራዊ መሻታችንን ማሳካት አያስችለንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የራስን መረጃ በራስ አቅም መሰብሰብና መተንተን ወሳኝ ግብዓት መሆኑን አመልክተዋል።
የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ሥራ በሀገር ልጆች እውቀትና ክህሎት ሲከወን ማየት ታላቅ ሀገራዊ ኩራት ነው ብለዋል፡፡
የመረጃ ትኩረታችን በቁጥር በሚገለጹ ውጤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ሰው ተኮር በሆኑና በዜጎች ሕይወት በሚታዩ ተጨባጭ ለውጦችም ላይ መሆን አለበት ነው ያሉት።

