Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ የዲጂታል እቅድ፣ ክትትልና ግምገማ ስርዓት ወጥነት ያለው የመረጃ አቀራረብ እንዲኖር አስችሏል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የዲጂታል እቅድ፣ ክትትል እና ግምገማ ስርዓት ወጥነት ያለው የመረጃ አቀራርብ እንዲኖር አስችሏል አለ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፡፡
”የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በሚል መሪ ሀሳብ ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ባስመዘገበችው ስኬት ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ጉባኤ ተካሂዷል።
በሚኒስቴሩ የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ከበደ በመድረኩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፥ ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ በመረጃና ስታቲስቲክስ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አሰራሮች ተግባራዊ ሆነዋል፡፡
ከሪፎርሙ በፊት የልማት አመላካች መረጃዎች አለመኖር፣ በየተቋማቱ የተበታተነና ወጥነት የጎደለው የዲጂታል ስርዓት እንዲሁም በወረቀት ላይ የተመሰረተ የመረጃ አያያዝ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስትቲዩት ጋር በመተባበር የዲጂታል እቅድ፣ ክትትልና ግምገማ ስርዓትን ማበልፀጉን ገልጸዋል፡፡
ይህ ስርዓት ተቋማት ወጥነት ያለው የመረጃ አቀራረብ እንዲኖራቸውና የእቅድ ክትትልና ግምገማ ሂደቶችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል በማድረግ ውሳኔዎቻቸው በመረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ አስችሏል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም እቅዶቻቸውን ሲያዘጋጁ ቀደም ሲል የነበራቸውን አፈፃፀም ከግምት እንዲያስገቡና አፈፃፀማቸውን በዲጂታል ስርዓት እንዲገመግሙ ያስቻለ መሆኑንም አብራረተዋል፡፡
ዘመኑ በደረሰበት የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የታገዘው ይህ የዲጂታል እቅድ፣ ክትትልና ግምገማ ስርዓት ግልፅና ጠቃሚ መረጃዎችን ማድረስ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ113 በላይ ተቋማትና ከ3 ሺህ በላይ የልማት አመላካች መረጃዎች በዚሁ ስርዓት አገልግሎት እያገኙ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ
Exit mobile version