Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከልን ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከል በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልክዕክት፥ መንግስት ለህዝብ የገባውን ቃል ይፈጽማል፤ የማይሰራውን ቃል አይገባም ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እንዲቻል ምርትን በብዛት ለማቅረብና የግብይት ማዕከላትን ለማስፋት የሚያከናውነው ስራ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ለከተማዋ 7ኛው ሲሆን፥ ለለሚ ኩራ፣ ለቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች ነዋሪዎች አማካይ በሆነው ሰሚት ዋና መንገድ ላይ መገንባቱ ነው የተገለጸው፡፡

ዘመናዊ ማሞቂያና ማቀዝቀዣ ያላቸው 221 መጋዘኖች፣ የችርቻሮ ሱቆች፣ ሱፐር ማርኬቶች እና ወፍጮ ቤቶችን ያካተተው ማዕከሉ በአንድ ጊዜ 250 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችል ፓርኪንግ እንዳለው ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡

በገበያ ማዕከሉ ማህበረሰቡ ለዕለት ፍጆታ የሚጠቀምባቸውን የሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ የበርበሬና የቅመማቅመም ምርቶችና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የአንድ ማዕከል የግብይት ስርዓት እውን አድርገናል ነው ያሉት።

በማዕከሉ የሚቀርቡ ምርቶች ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንዳላቸው የገለጹት ከንቲባዋ፥ ዋጋ የሚያንረውን ህገወጥ የደላላ ሰንሰለት በመበጣጠስ ከአምራቹ ያልተቋረጠ ምርት በማቅረብ የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና የሚያቃልል ነው ብለዋል።

ከተለያየ ቦታ በኮሪደር ልማት የተነሱ ነዋሪዎችንና የገበያ ማዕከሉ ያረፈበትን መሬት ለልማት የለቀቁ አርሶ አደሮች በማዕከሉ ሱቅ እንዲያገኙ መደረጉን አንስተዋል፡፡

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው ማዕከሉ ተገንብቶ ወደ ሥራ እንዲገባ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version