አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለማችን ግዙፍ አውሮፕላን አምራች የሆነው ቦይንግ ኩባንያ ከፍተኛ አመራሮች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የ80 ዓመታት ስኬታማ ጉዞ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቦይንግ ኩባንያ የኮሜርሻል አውሮፕላኖች ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቴፋኒ ፖፕ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ ጉዞ ለአቪዬሽን ዘርፍ ተዋናዮች በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በቦይንግ እና መላው የኩባንያው አባላት ስም 80 ዓመታትን በአቪዬሽን መሪነት፣ በስትራቴጂካዊ እድገት እና ተሸላሚ በሆነው አገልግሎቱ ለዘለቀው ኢትዮጵያ አየር መንገድ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
በኩባንያው የንግድ አውሮፕላኖች የአቅርቦት ሰንሰለትና ማምረቻ ከፍተኛ ም/ፕሬዚዳንት ኢህሳን ሙኒር በበኩላቸው÷ ለመላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን አባላት “መልካም 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል” እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አህጉር ያለውን የአቪዬሽን መሪነት ሚና አድንቀው÷ ይህንን ታላቅ ታሪካዊ ምዕራፍ በጋራ መዘከር መቻል ትልቅ ክብር እንደሆነ ገልጸዋል።
በአየር መንገዱ እና በቦይንግ መካከል ላለው የረጅም ጊዜ የንግድ ትስስር እና አጋርነት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ደግሞ የኩባንያው አውሮፕላን ፕሮግራሞች ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ማይክ ፍሌሚንግ ናቸው።
ይህ አስደናቂ ስኬት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን የገለጹት አመራሮቹ÷ የተቋማቱ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ቦይንግ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ አጋርነት ያላቸው ሲሆን÷ አየር መንገዱ ዘመናዊ የቦይንግ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በአፍሪካ ቀዳሚው እና ግዙፉ አየር መንገድ መሆኑ ይታወቃል።
በዮናስ ጌትነት

