Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በርትተን ከሰራን ሀገራችን ለአፍሪካ ተምሳሌት ትሆናለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በርትተን ከሰራን እና ከተጋገዝን ሀገራችን ለአፍሪካ ተምሳሌት ትሆናለች አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካን መርቀው አገልግሎት ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በርትተን ከሰራን ብልጽግናን ሙሉ ለሙሉ ማየት እንችላለን ብለዋል።

የግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካ ለአገልግሎት መብቃት ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፋብሪካዎች መገንባት እና ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ በመላ ሀገሪቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በተግባር ያረጋገጠ እንደሆነ ተናግረዋል።

በምስራቅ ሸዋ አካባቢ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን ተዟዙረው መመልከታቸውን ጠቅሰው፤ በዶሮ እርባታ እንዲሁም በእንስሳት ልማት በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢው ልማት የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡

በዚህም በአካባቢው የሚመረተው እንቁላል እና ወተት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝም ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ ግብርናውን በማዘመን በትራክተር የማረስ ጥሩ ጅምር ላይ መሆኑን አድንቀው፤ አሁን ላይ በበሬ የሚያርሱ አርሶ አደሮች ወደ ትራክተር እርሻ እንዲገቡ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በበሬ የሚያርሰው አርሶ አደር ህይወት እስኪለወጥ ድረስ እንቅልፍ መተኛት መታሰብ የለበትም ብለዋል፡፡

ስራን መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ ባህል መሆኑ ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህ ባህል ውጤት የሚያመጣ መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገራችን የመበልጸግ እና የመለወጥ ሰፊ ዕድል አላት ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በርትተን ከሰራን፣ ከተጋገዝን እና መደማመጥ ከቻልን ሀገራችን የበለጸገች እና ለአፍሪካ ተምሳሌት ትሆናለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትክክለኛ መስመር ላይ መሆኗን ገልጸው፤ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት አመልክተዋል።

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version