Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መፈፀም ይገባል – ጀኔራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ በፍፁም ሕዝባዊነት እና በወታደራዊ ፕሮፌሽናሊዝም መፈፀም ይገባል አሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ።

በሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ20ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ሰላም አስከባሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

ጀኔራል አበባው ታደሰ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ተመራቂዎች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት በመፈፀም የሠራዊቱን መልካም እሴቶች መሠረት በማድረግ በግጭቶች ተጎጂ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም ባበረከተችው አስተዋፅኦ ስሟ በደማቅ ቀለም እንደተጻፈ አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት 80ኛ የምስረታ በዓል ላይ የተሰጣት ዕውቅና የዚህ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በዓለም አቀፍ፣ በአህጉር እና በቀጣናው እያደገና ውስብስብ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ይህም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ጋር በቀጥታ ቁርኝት እየፈጠረ በመሄዱ በላቀ ዝግጁነትና ብቃት ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን የመከላከያ ሰራዊት ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

በሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የኮሙኒኬሽን እና ሚዲያ ኃላፊ ሻለቃ አክሊለ ለገሰ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሥር በሶማሊያ “አውስኦም” እና በአፍሪካ ሕብረት ስር በደቡብ ሱዳን “ዩናሚስ” ለሚሰማሩት ክፍሎች የቅድመ ስምሪት ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር በአስተማማኝ ሁኔታ ከመጠበቅ ጎን ለጎን በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ እያበረከተ ያለውን ሚና አጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

Exit mobile version