አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለሕዝብ ማስተዋወቅ የቻሉበትን መድረክ በመፍጠር በኩል ተጨባጭ ተግባራት ተከናውነዋል አሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦቻቸውን ለሕዝብ በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው መድረክ ለምርጫ ክርክሩ በ19 ዙር ያካሄዱ ሲሆን ÷ክርክሩም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ዲጂታል አማራጮች ለመራጩ ሕዝብ ተደራሽ ተደርጓል።
ወ/ሮ ሜላትወርቅ ሀይሉ÷በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለሕዝብ ማስተዋወቅ የቻሉበትን መድረክ መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል።
መራጩ ሕዝብም በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ድምፅ በመስጠት ወኪሎቹን እንዲመርጥ ለማስቻል የምርጫ ቅስቀሳና ክርክር ክህሎት ማዳበሪያ የተግባር ልምምድ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል።
በፖሊሲ ጥናት ምሁራንና ሙያተኞች በመታገዝ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አማራጭ ሃሳብ ልዩነትና ተመሳሳይነት የሚለካበትን መረጃ የመሰብሰብ ሥራ በጥንቃቄ መሰራቱን ተናግረዋል።
የክርክር ሒደቱን ቅርፅ ውጤታማነት ለማስጠበቅ የሚዲያና ኮሙኒኬሽ ሙያተኞች የተሳተፉበት ተከታታይ ውይይት በማድረግ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከተለምዷዊ ክርክር ወጣ ያለ ክርክር አካሂደዋል ነው ያሉት፡፡
የክርክር ሒደቱ ተጋባዥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ገለልተኛ ተቋማት ወኪሎችም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ የሚያቀርቡበት ዕድል እንደተፈጠረ አንስተዋል።
በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከታዳሚ በሚቀርብላቸው ጥያቄ የሕዝብን ፍላጎት በመረዳት መለካት የሚችሉበትን የክርክር ቅርፅ መስጠት እንደተቻለ አብራርተዋል።
የክርክር መሪዎችም ረጅም ጊዜ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን የሰሩና ገለልተኝነታቸውን ለማረጋገጥ ለፓርቲዎች በመላክ አስተያየት እንዲሰጡበት መደረጉን ጠቅሰዋል።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ፖሊሲና የፕሮግራም ዓላማ ለሕዝብ በግልፅ በማስተዋወቅ መራጮች በቂ ግንዛቤ የሚያገኙበትን ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።
በምርጫ ሒደቱ የጥሞና ጊዜም ዜጎች በየቤታቸው ለማን ድምፅ መስጠት እንዳለባቸው ሃሳብ የሚያሰላስሉበትና ፓርቲዎችም ዕጩዎች ያለውን ድባብ የሚከታተሉበት እንደሆነ መጠቆማቸውንም ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡
በቀጣይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒ፣ ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከጥዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው ምርጫም የአፍሪካ ሕብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የሀገር ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በታዛቢነት እንደሚታደሙ አስታውቀዋል።
የምርጫ ሒደቱን ለመጎብኘት ጥያቄ ያቀረቡ 16 የዲፕሎማቲክ ማሕበረሰብ አባላትንም ምላሽ ለመስጠት በሒደት ላይ መሆናቸውንም ሰብሳቢዋ አስረድተዋል።

