Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የምርጫ ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ ጥቆማ ማድረጊያና ምላሽ መስጫ ሥርዓት ተቋቋመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዜጎች ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር የተያያዙ ችግሮችንና ክስተቶችን ደኅንነቱ በተጠበቀና ፈጣን በሆነ መንገድ ጥቆማ የሚያደርጉበትን “ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ችግሮች ሪፖርት ማድረጊያ እና ምላሽ መስጫ ሥርዓት” ዘርግቷል።

ይህ ሥርዓት ምርጫ ቦርድ፤ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት መረጃዎችን አስቀድመው እንዲያገኙ፣ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ እንዲሁም ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ ለማገዝ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

ምን ዓይነት ችግሮችን ጥቆማ ማድረግ ይችላሉ?

• በምርጫ ሂደቶች ላይ የሚፈጠሩ መስተጓጎሎች፣

• በድምፅ አሰጣጥ ወይም በቆጠራ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች፣

• በምርጫ ጣቢያዎች አቅራቢያ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች፣

• በመራጮች ላይ የሚደርስ ማስፈራራት ወይም ትንኮሳ፣

• በምርጫ ቁሳቁስ ላይ የሚደርስ ጉዳት፣

• ዐመፅ ወይም ዛቻዎች፣

• ውጥረት የሚፈጥሩ የሐሰት መረጃዎች፣

• እንዲሁም ምርጫውን ሊያስተጓጉል የሚችል ወይም ማንኛውም ሌላ አጠራጣሪ ድርጊት ጥቆማ ማድረግ ይችላሉ።

መቼ ጥቆማ መስጠትይኖርብዎታል?

• የምርጫ ሂደቶች ሲስተጓጎሉ ሲመለከቱ፣

• ከላይ የተጠቀሱትን ክስተቶች በቀጥታ ከተመለከቱ፣

• የዐመፅ ወይም የግጭት ሥጋት ካለ፣

• እንዲሁም አስቸኳይ ዕርምጃ የሚያስፈልጋቸው ማንኛውም ምርጫን የሚያውኩ ክስተቶች ከተመለከቱ።

ችግሮችን አስቀድሞ ሪፖርት ማድረግ ሁኔታዎች እንዳይባባሱ ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ይረዳል።

እንዴት ጥቆማ መስጠት ይችላሉ?

በሚከተሉት መንገዶች ጥቆማ መስጠት ይችላሉ፦

• በነፃ የስልክ መስመር 6214 ላይ በመደወል

• አጭር የጽሑፍ መልዕክት ወደ 7555 በመላክ

ሪፖርት ሲያደርጉ የሚከተሉትን መረጃዎች ለማካተት ይሞክሩ፦

• ምን እንደተከሰተ

• የት እንደተከሰተ

• መቼ እንደተከሰተ

• ማን እንደተሣተፈበት (የሚታወቅ ከሆነ)

ማን ጥቆማ መስጠት ይችላል?

ማንኛውም ሰው ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክስተቶችን ጥቆማ መስጠት ይችላል፤ ከእነዚህም መካከል፦
• ዜጎች፣

• የምርጫ ታዛቢዎች፣

• የፖለቲካ ፓርቲዎች፣

• የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣

• የሴቶችና የወጣቶች ማኅበራት፣

• ምርጫ አስፈጻሚዎች፣

• የቦርዱ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ጥቆማ

ጥቆማ ከተሰጠ ካደረጉ በኋላ ምን ይከናወናል?

1. ጥቆማዎ እኛ ጋር ከደረሰ በኋላ ይመረመራል፣

2. የቀረበው መረጃ ትክክለኛነት ይረጋገጣል፣

3. እንደ አስፈላጊነቱ ምርጫ ቦርድ እና የሚመለከታቸው ተቋማት በቅንጅት ምላሽ ይሰጣሉ።

4. የተወሰደው ዕርምጃ ወይም የተሰጠው ምላሽ ለጥቆማ አቅራቢው ሊገለጽ ይችላል፣
የእርስዎ ጥቆማ መስጠት ለምን አስፈለገ?

የሚያቀርቡት ጥቆማ ለሚከተሉት ጉዳዮች ይረዳል፦

• የምርጫውን ግልጸኝነት ለማሻሻል፣

• ሰላማዊ እና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ ለማገዝ፣

• መራጮችን እና የምርጫ አስፋጻሚዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ፣

• ዐመፅ እና ግጭቶችን ለመከላከል፣

የምርጫውን ሂደት ሊያስተጓጉል የሚችል ማንኛውንም ችግር ካዩ ወይም ካጋጠመዎት እባክዎን ወዲያውኑ ጥቆማ ይስጡ!
እያንዳንዱ ጥቆማ ይበልጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ የምርጫ ሂደት እንዲኖር አስተዋፅዖ ያበረክታል።

የመገናኛ መንገዶች

ነፃ የስልክ መስመር 6214
አጭር የጽሑፍ መልዕክት 7555
አድራሻ: የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ| አዲስ አበባ
ድረ-ገጽ www.nebe.org.et

Exit mobile version