አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ አሞላል እና ውሃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ የሚያደርጉት የሶስትዮሽ ስብሰባ መስከረም ወር ላይ እንደሚቀጥል የውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ የሶስቱ ሃገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትናንትናው እለት ስብሰባ ማካሄዳቸውን አስታውቋል፡፡
በስብሰባው ላይ የሂደቱ ታዛቢ የሆኑት የደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካ ተወካዮች እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት የተወከሉ ባለሙያዎች መሳተፋቸውንም ገልጿል፡፡
በወቅቱም ላላፈው አንድ ሳምንት በሃገራቱ ባለሙያዎች በታላቁ የህዳሴ ግድብ አሞላልና የውሃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ ሲከናወን የነበረው የባለሙያዎች ድርድር ሪፖርት መቅረቡንም ጠቅሷል፡፡
በቀጣይ የሚኖረውን ሂደት በሚመለከትም ሃገራቱ የድርድሩን ሂደት የሚገልጽ ደብዳቤ ለደቡብ አፈሪካዋ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀ መንበር ዶክተር ናዴሊ ፓንዶል ለመላክ መስማማታቸውንም ነው የገለጸው፡፡
በዚህም ሱዳን የምትሰጠው ማረጋገጫ እንደሚጠበቅ የገለጸው ሚኒስቴሩ የሶስትዮሽ ስብሰባው መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

