Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች የፎረንሲክና የሥነ ምረዛ ምርመራ ልሕቀት ማዕከልን መረቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታልን ዘመናዊ የፎረንሲክ (ዲ ኤን ኤ) እና የሥነ ምረዛ ምርመራ ልሕቀት ማዕከልን መርቀዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የልሕቀት ማዕከሉ በሳይንሳዊ መንገድ የተሟሉና ዘመኑን የዋጁ መሳሪያዎችን የያዘ ነው፡፡

አንጋፋው ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ከ116 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አውስተው÷ ይሁን እንጂ ዘመናዊ መሳሪያዎች ያልተሟሉለት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

የለውጡ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረትም ዘመናዊ መሳሪያዎች ተሟልተውለት የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት ።

በሌላ በኩል የልሕቀት ማዕከሉ የአስክሬን ምርመራ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ከንቲባዋ አስረድተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ÷ ማዕከሉ የፎረንሲክ፣ የዘረመልና የሥነ ምረዛ አገልግሎትን በአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል።

በሀገሪቱ የፎረንሲክ የምርመራ ተቋማት 5 ብቻ እንደሆኑ ያነሱት ሚኒስትሯ÷ በዘመናዊ መንገድ የተደራጀው የልሕቀት ማዕከሉ ለከተማዋ ብሎም ለሀገሪቱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ 80 የአስክሬን መመርመሪያ መሳሪያዎች መያዙን ጠቁመው÷ ይህም ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት የፍትሕ ሥርዓቱን ከፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በቅድስት ብርሃኑ

Exit mobile version