Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዜጎችን አቅም ያማከለ የመኖሪያ ቤት ግንባታ አማራጭን ማስፋት ይገባል – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከዚህ በፊት በተለመደው የመኖሪያ ቤት አሰራር ሒደት በከተሞች ያለውን የቤት አቅርቦት ችግር መፍታት አይቻልም አሉ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅግ ዘመናዊና ፈጣን የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም የተገነቡ ቤቶችን የሚያሳይ የግንባታ ሳይት በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል፡፡

ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ጉብኝቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ የለውጡ መንግሥት ለከተሞች እድገት በሰጠው ትኩረት ዘርፈ ብዙ ትሩፋት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በተከናወነው ሥራ ከተሞች የድህነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና የሥራ አጥነት መገለጫ ናቸው የሚለውን አሉታዊ ትርክት መቀየር መቻሉን አመልክተዋል፡፡

አሁን ላይም ከተሞችን የብልጽግና ማሳያ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት፡፡

ለአብነትም አዲስ አበባን ጨምሮ በ67 ከተሞች እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተሞችን ጽዱ፣ ምቹና ለኑሮ ተስማሚ አድርጓል ብለዋል፡፡

በከተሞች የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቤቶች ፖሊሲን በማጽደቅ ለመተግብር እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ዘመኑን የዋጀና የዜጎችን የእድገት ፍላጎት የሚመጥን የቤት አቅርቦት ለማሟላት በቅንጅትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በተለመደው የቤት አሰራር ሒደት የቤት አቅርቦት ችግርን መፍታት እንደማይቻል ጠቁመው÷ የተለያዩ የግንባታ አማራጮችን መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት 16 እና 17 ዓመታት 160 ሺህ ገደማ የሚሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ብቻ መገንባት መቻሉን አንስተው÷ በአሁኑ ወቅት ባለፉት አምስት ዓመታት ግን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ቤቶች መገንባታቸውን አብራርተዋል፡፡

እነዚህ ቤቶች በዜግነት አገልግሎት፣ በበጎ ፈቃድ፣ በማህበራዊ ተሳትፎና በተለያዩ አማራጮች መገንባታቸውን አመልክተዋል፡፡

አሁንም በከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆኑ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዚህ መሰረትም የዜጎችን የመግዛት አቅም ያማከለ የመኖሪያ ቤት ግንባታ አማራጭን ማስፋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ተጀምረው የማያልቁ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችና ዜጎችን ለከፍተኛ እዳ የሚዳርጉ ፕሮጀክቶች እንዳይኖሩ ሰፊ ጥናት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

እጅግ ዘመናዊና ፈጣን የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም በርካታ ቤቶችን ለመገንባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለአብነትም የ3ዲ ኮንክሪት ህትመት፣ የቅድመ ዝግጅት ቀላል የአረብ ብረት ግንባታና የኮንቴይነር መኖሪያ ቤቶች የላቁ የግንባታ ዘዴዎች በጥምረት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የተገጣጣሚ ብረት የቤት ግንባታና ሌሎች መሰል የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም የመኖሪያ ቤቶችን ተደራሽነት ለማስፋት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version