አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው የሕልውና ጉዳይና የሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረት ነው አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት የእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር አካሂዷል።
አቶ አደም ፋራህ መድረኩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት÷ መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ተቋማት በጋራ ጥረትና በብዙ መስዋዕትነት የተመዘገቡ ሀገራዊ ድሎችን ዕውቅና የመስጠት ልምድ ማዳበራቸው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽዖ የሚያበረክት ሊለመድና ሊቀጥል የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው የሕልውና ጉዳይና የሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረት መሆኑን ጠቅሰው÷ የተለያዩ የብዝኃነት መልኮች የምናስተናግድበት፣ ዘላቂ ሰላም የምናረጋግጥበት እና ጠንካራ ሀገር የምንገነባበት ምሰሶ ነው ብለዋል።
በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች አዎንታዊ ተሳትፎና አስተዋጽዖ የማይተካ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።
ድርጅቶቹ መራጩን ሕዝብ ከማስተማር፣ ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን የመምረጥ መብቱን እንዲጠቀም በማድረግ እንዲሁም በሰላም እሴት ግንባታ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ድልድይ በመሆን የዜጎችን ተሳትፎና ባለቤትነት ከማረጋገጥ አኳያ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረክታሉም ነው ያሉት።
በቀጣይም የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች በሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የድርሻቸውን እንዲያበረቱ ብልጽግና ፓርቲ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመርሐ ግብረ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በአድማሱ አራጋው

