አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሩዝ ልማት የተመዘገበውን አስደናቂ ለውጥ ለማስቀጠል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰራ ይገባል አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡
ሚኒስቴሩ የሩዝ ልማት በብሔራዊ ፍላግሺፕ ፕሮግራም ደረጃ ከተያዘ ጀምሮ ያለውን የ2 ዓመት ተኩል የሩዝ ዕቅድ አፈፃፀም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት አካሂዷል፡፡
በሚኒስቴሩ የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ደሳለኝ ተሻለ በዚህ ወቅት ÷ ሩዝ በ10 ዓመቱ የግብርና መሪ ዕቅድ በትኩረት ሊሰራባቸው ከተለዩ የግብርና ምርቶች አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሩዝ ልማት ላይ በትኩረት በመሰራቱ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
ለአብነትም በአነስተኛ አርሶ አደር በመኸር ሩዝ በ2012 ዓ.ም ይለማ ከነበረው 60 ሺህ ሄክታር መሬት በ2017 ዓ.ም ወደ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር ማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርት በ2017 ዓ.ም ወደ 62 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ማሳደግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
ከውጭ የሚገባው የሩዝ ምርት በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 13 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በ2017 ወደ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን እንደቀነሰና በዚህም 442 ሚሊየን ዶላር ማዳን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በሩዝ ልማት የተመዘገበውን አስደናቂ ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመስራት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።

