አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በ2018 በጀት ዓመት 163 ተቋማትን ኦዲት አድርጌያለሁ አለ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 26ኛ መደበኛ ጉባዔው የተቋሙን ሪፖርት አድምጧል፡፡
በዚህም መስሪያ ቤቱ ዓመታዊ የመንግሥት ባለበጀት ተቋማትን ሒሳብ የፋይናንሻል፣ የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
የፌደራል ዋና ኦዲተር ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በዚህ ወቅት÷ በበጀት ዓመቱ 163 ተቋማትን ኦዲት በማድረግ እቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በመንግሥት ተቋማት የበጀት አጠቃቀም ላይ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አሰራር የመተግበር ሒደት ለኦዲት ሥራው አጋዥ እንደነበር አመላክተዋል።
በተለያዩ ተቋማት አሁንም የበጀት አጠቃቀም ክፍተት መኖሩን ጠቁመው÷ በየተቋማቱ የታዩ የኦዲት ግኝቶችን ለምክር ቤቱ በዝርዝር አቅርበዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ

