አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሳይበር ጥቃትን በመከላከል ሀገራዊና ተቋማዊ ዲጂታል ሃብቶችን ነቅቶ መጠበቅ ዘመኑ የሚጠይቀው ሥራ ነው አሉ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ።
የመከላከያ ሳይበር ማዕከል ያሰለጠናቸውን መሰረታዊ የሳይበር ሰልጣኞች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት÷የሳይበር ምሕዳርን በማሥፋት የሀገርን ህልውና ሊፈታተኑ የሚችሉትን ቀን ከሌት በንቃት መጠበቅ ያስፈልጋል።
መከላከያ ሠራዊት ዘመኑ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር ራሱን እያዋሃደ መሆኑን ገልጸው÷ ሠራዊቱ በሳይበር ምህዳር ያለውን ዝግጁነት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል።
ሠራዊቱ ከለውጡ ወዲህ በባሕር ኃይል እና በሳይበር ምህዳር አደረጃጀቱን በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል የሚቃጡ ውስጣዊና ውጫዊ ጥቃቶችን በብቃት ማክሸፍ መቻሉን አብራርተዋል።
አሁን ላይ የዲጂታል አሰራሮች እየሰፉና እየተቀየሩ በመሆናቸው የሳይበር ማዕከሉም የተቋሙን ሀብትና ደህንነት ለመጠበቅ የማሰልጠን ተግባሩን ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሳይበር ጥቃት የጦር ሜዳውን የውጊያ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈታተን በመሆኑ ሀገራዊና ተቋማዊ ዲጂታል ሀብቶችን 24 ሰዓት ነቅቶ መጠበቅ ዘመኑ የሚጠይቀው ሥራ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ተመራቂዎች የሳይበር ሠራዊት መሆናቸውን በመገንዘብ የገበዩትን እውቀት በከፍተኛ ዲሲፕሊንና ኃላፊነት መጠቀም እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጅታል ገልጿል።

