አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ መድረክ የሚያጣምረውንና በአፍሪካ ቀዳሚ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷“ዲጂታል ለልህቀት” በሚል ስያሜ በተዘጋጀው ጉባዔ ላይ በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ መድረክ የሚያጣምር እንዲሁም በአፍሪካ ቀዳሚ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያን መርቀን ሥራ አስጀምረናል ብለዋል፡፡
ይህ ታላቅ ስኬት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ኩራት ከመሆኑም በላይ በቴክኖሎጂ የሚመራ እና ዓላማ ተኮር ኢንቨስትመንት ምን ሊያስገኝ እንደሚችል ማረጋገጫ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
የኢኮኖሚ ወሳኝ መሠረተ ልማት የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን ጊዜ ይቆጥባል፤ የሙስና ቀዳዳዎችንም ይደፍናል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ባለፈም በመንግሥት በኩል የተቋማትን ታማኝነት እና ጥንካሬ እንደሚያጎለብት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ትልሞች ተራ ምኞት ሳይሆኑ በራሳችን እጆችና አቅም የምንገነባቸው እውነታዎች መሆናቸውን በግልጽ የሚያሳይ ምስክር ነው ብለዋል።
ይህን ስኬት እንዲጠናከር፣ ተሞክሮውን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንድናካፍል እንዲሁም ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት እንጓዝ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

