አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመፍታት ተግባራዊና አዲስ የፈጠራ መፍትሄዎችን በጋራ መተግበር ይገባል አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ32 ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።
ሚኒስትሩ በለንደን የአየር ንብረት የድርጊት ሳምንት ማስጀመሪያ ላይ በለንደን ስቶክ ኤክስቼንጅ በመገኘት የዕለቱን ግብይት በይፋ ከፍተዋል፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ምላሽ የመስጠትን አስቸኳይ አስፈላጊነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም በታሪኳ ከፍተኛ ሙቀት ከሚመዘገብባቸው ሳምንታት አንዱን እያስተናገደች መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም የአየር ንብረት ለውጥ እያመጣ ያለውን ፈጣን ተፅዕኖ በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
መሰል ሁነቶች ተዓማኒነት ያለውና የጋራ የአየር ንብረት ለውጥ ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ያመላክታሉ ያሉት ሚኒስትሩ÷ ማንኛውም ሀገር ብቻውን የተጋረጠውን ቀውስ በተሳካ ሁኔታ መፍታት እንደማይችል አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመድረኩ ላይ የታደሙ ኃላፊዎች፣ ተቋማት፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ተግባራዊና አዲስ የፈጠራ መፍትሄዎችን በጋራ ለማዘጋጀት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ጠንካራ አጋርነትን እንደሚያሳድጉና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ፈተናዎችን ለመፍታት፣ የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ልማትን ለመደገፍ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን እንደሚያመነጩ አመልክተዋል።
ለመላው ዓለም የሚጠቅሙ መፍትሄዎችን ለማዘጋጀት ሀብታችንን፣ የጋራ እውቀታችንን እና የጋራ ቁርጠኝነታችንን ጠምረን መተግበር አለብን ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

