Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ሥነ ምህዳር የሀገር ሉዓላዊነት መሠረታዊ ምሰሶ ነው – ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ለሀገራዊ ልማትና ለብሔራዊ ደህንነት ቁልፍ ስትራቴጂ በማድረግ ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ነው አሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ።

3ኛው ዓለም አቀፍ የሳይበር ደህንነት እና ሰውሰራሽ አስተውሎት ጉባዔ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል፡፡

ዳይሬክተሯ በዚህ ወቅት ÷ የሳይበር ደህንነት አሁን ላይ ከቴክኒክ ስራነት ወደ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂካዊ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሸጋገሩን አመልክተዋል፡፡

ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ሥነ ምህዳር የሀገር ሉዓላዊነት መሠረታዊ ምሰሶ መሆኑን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያም አስተማማኝ ዲጂታል ምሕዳር ለመገንባት ቁርጠኛ ናት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2004 ዓ.ም ያወጣችውን የመጀመሪያውን ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ዘመናዊ ስጋቶችን እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ታሳቢ በማድረግ በ2017 ዓ.ም በድጋሚ ማሻሻሏን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የቁልፍ መረጃ መሠረተ ልማት ጥበቃ፣ የግል መረጃ ጥበቃ፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትና የሳይበር ወንጀል ጥበቃ አዋጆችን ጨምሮ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

ይህም ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ምሕዳር ለመገንባት፣ ለሀገራዊ ልማት ስኬት እና ለውጭ ኢንቨስተሮች እምነት መጎልበት መሰረታዊ ምሰሶ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዘመን በየነ

Exit mobile version