አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በፈተናዎች እያለፈች በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ ለመጪው ትውልድ የሚጨበጥ ተስፋን ለማስረከብ በስፋት ሰርታለች። በሕዝብ አቅምና በአመራር ቁርጠኝነት ታላላቅ የስኬት ምዕራፎችን እያስመዘገበች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት “ከለውጥ ወደ ዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው “ኢትዮጵያ ታከናውናለች” ብሔራዊ ጉባዔ ይህንን የለውጥ ጉዞ በጥልቀት የፈተሸና ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሠረት ለመጣል ትልም የተነደፈበት ታሪካዊ ክስተት ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በራስ አቅም እውን ማድረግን ጨምሮ በርካታ ድሎችን አስመዝግባለች። በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በአይሲቲ ዘርፎች በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
በግብርና ዘርፍ የስንዴ ምርትን ከውጭ ማስገባትን ከማስቀረት ባሻገር ወደ ውጭ መላክ የተጀመረበት አስደናቂ ውጤት ተመዝግቧል። በጋ ከክረምት ማሳዎች ጾም እንዳያድሩ በቆራጥ አመራር በተከወነው ሥራ ኢትዮጵያ ከአህጉሩ ቀዳሚ የስንዴ አምራች ሀገር ለመሆን በቅታለች።
በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት መጣል፣ የሥርዓተ ምግብን ማሻሻል እንዲሁም የህብረተሰቡን ገቢ በማሻሻልና ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በመርሐ ግብሩ ትኩረት በተሰጣቸው የወተት ላሞች ልማት፣ የዶሮ እርባታ እና ንብ ማነብ የግብርና መስኮች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል። በዝርያ ማሻሻል ላይ በተሰራው ስራ ሀገራዊ የወተት ምርታማነት ከእጥፍ በላይ የጨመረ ሲሆን፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ16 ቢሊየን ሊትር በላይ የወተት ምርት ተገኝቷል።
በዶሮ ስጋ እና በእንቁላል ምርትም ተመሳሳይ ስኬት በመመዝገቡ የምርት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል።
በንብ ማነብ ስራ እንዲሁ አመርቂ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ÷ የማር ምርታማነት በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል።
ሌላው በግብርናው መስክ ኢትዮጵያ የላቀ ስኬት ያስመዘገበችው በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሲሆን፤ መርሐ ግብሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እየተተገበረ እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ በመስጠት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አረዓያ መሆን ተችሏል።
ኢትዮጵያ መጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ይረከብ ዘንድ ሳትታክት እየተጋች እንደ ግብርናው ዘርፍ ሁሉ በሁሉም መስኮች አስደናቂ ስኬቶችን እየጨበጠች ነው።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በመንግሥት በተሰጠው ትኩረት ከስራ ውጪ ሆነው የነበሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ተመልሰው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። በዘርፉ ላይ በተካሄደው ሪፎርም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የዘርፉን አቅም ማውጣት ተችሏል።
በተለይም በተኪ ምርት ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ወጪ ማስቀረት ተችሏል።በኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባትም ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ተፈጥሯል።
ሌላው በኢትዮጵያ ማከናወን የላቀ ስኬት ከተመዘገበባቸው መስኮች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ ነው።
ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ የቱሪስት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እና የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ የተሰራው ስራ ውጤቱ ባለፉት ዓመታት ታይቷል።
በዚህ ረገድ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ የተሰሩ ሥራዎች የቱሪስቶችን ቀልብ ለመሳብ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
አዲስ አበባ ከተማን እንደስሟ አበባ ለማድረግ የተሰራው ስራም ቱሪዝምን በተለይም የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማጎልበት በኩል የማይናቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ይታወቃል።
በማዕድን ዘርፉን ተደብቆ የነበረውን የዘርፉን አቅም የመግለጥ ሥራ ተሰርቷል። በዚህም በወርቅ ብቻ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል።
ሌላው በኢትዮጵያ እጅግ ተዘንግቶ የነበረው ጉዳይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሲሆን፤ ባለፉት ዓመታት በተሰጠው ትኩረት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ አስደናቂ ውጤት አምጥቷል።
ለቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት በተለይም አገልግሎትን ለማዘመን የሚደረገው ጥረት እያገዘ ነው።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰራ መሆኑ የኢትዮጵያን የማከናወን አቅም በእጅጉ እየደገፈ ነው።
እነዚህ የለውጡ ውጤቶች የተሳኩት በአጋጣሚ ሳይሆን በመደመር እሳቤ በተፈጠረው የአመራር ትኩረትና ቁርጠኝነት መሆኑ ግልጽ ነው።

