Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን የካርበን ገበያ እድሎች ለማስፋት…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ልማት ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የአየር ንብረት ለውጥ ርምጃዎች በሀገር አቀፍ የልማት ዕቅዶች ውስጥ መካተታቸው ወሳኝ ሚና አለው አለ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፡፡

የኢትዮጵያ ካርበን ገበያ ለዘላቂ የግብርና ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም እና ለገጠር ትራንስፎርሜሽን ያለውን ዕድል እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ስዩም መኮንን በዚህ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ የኢትዮጵያ ግብርና ልማት ስጋት መሆኑን ጠቁመው ÷የአየር ንብረት ለውጥ ርምጃዎችን በሀገር አቀፍ የልማት ዕቅዶች ውስጥ ማካተቱ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተለያየ መልክዓ ምድር እና የግብርና ሥርዓት እንዲሁም ልዩ ልዩ አሰራሮች አሏት ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷ ምህዳሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስና ሥራዎችን ለመተግበር ሰፊ ዕድል እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

‎የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ኢያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ የካርበን ፋይናንስ ዕድሎችን ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ጋር ማቀናጀት ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል።

የካርበን ገበያ ዘላቂ የግብርና አሠራሮችን ለመደገፍ፣ የአፈርን ጤንነት ለማሻሻል፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት እና ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ የገቢ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያስችል አዲስ የፋይናንስ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ የሀገርን መልክዓ ምድር ለመለወጥና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ እየተደረገ ያለ ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ መሆኑን ገልጸው ÷ ይህም በካርበን ገበያ ተሳትፎ ውስጥ ያሉ ዕድሎችን ለመመርመር ጠንካራ መሠረት ይጥላል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ አዲስ እየታዩ ባሉ የአየር ንብረት ፋይናንስ ሥርዓቶች ውስጥ የምታደርገውን ተሳትፎ ለመምራት የሳይንስ፣ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ያላቸው ሚና ጉልህ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት በላይ ካሳ (ፕ/ር) ናቸው።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያን የአየር ንብረትና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ግቦች ለማሳካት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ትብብር ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ምሁራን፣ የልማት አጋሮች፣ የግል ዘርፍ ተወካዮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version