Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) «መደመር» መጽሐፍ በቻይንኛ ተተርጉሞ ለንባብ ሊበቃ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) «መደመር» መጽሐፍ በቻይንኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በቅርቡ ለንባብ ሊበቃ ነው፡፡

በ2010 ዓ.ም የነበረውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ የኢትዮጵያ የነገ ጉዞ ፍኖተ ካርታ ሆኖ የተወለደውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የተጻፈው የ«መደመር» መጽሐፍ የቻይንኛ ቋንቋ ትርጉም ሥራው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

መደመር ባለፉት አሥርት ዓመታት ከአፍሪካ አህጉር ፈልቀው ወደ ዓለም መድረክ ከተሻገሩ ጥቂት ሀገር በቀል ፍልስፍናዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እሳቤ የሆነውን የመደመር ፍልስፍና በርካቶች በትኩረት የሚመለከቱት አጀንዳ እየሆነ መጥቷል፡፡

ቻይና የትርጉም ሥራውን እያጠናቀቀች ባለችበት በዚህ ወቅት መጽሐፉ ከዚህ ቀደም በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በእንግሊዝኛ ካለው ተደራሽነት በተጨማሪ በቅርቡ በዓረብኛ እና በፓኪስታን የኡርዱ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በደማቅ ሁኔታ መመረቁ ይታወሳል።

አሁን ደግሞ በቢሊየኖች የሚነገርለትን የቻይናን መድረክ በይፋ ለመቀላቀል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው፡፡

ይህ የ«መደመር» መጽሐፍ ወደ ቻይንኛ ቋንቋ መተርጎም እና አሁን ላይ ሀያል ከሆኑ ሀገራት መካከል የምትጠቀሰውን ቻይናን ትኩረት ማግኘቱ ከመጽሐፍ ትርጉም ሥራ ባለፈ በርካታ ስትራቴጂካዊ እና ፖለቲካዊ እንድምታዎችን ይዟል፡፡

እንደ ቻይና ዓይነት እጅግ የዳበረ፣ የረጅም ዘመን የፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ ያላት እና ከማኦ ዜዱንግ እስከ ዴንግ ዚያኦፒንግ አሁን ደግሞ እስከ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የዘለቀ የራሷ የርዕዮተ ዓለም መስመር ያላት ሀገር፣ “መደመር”ን ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ ወደ ራሷ ቋንቋ መተርጎሟ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪና ትኩረት ሳቢ ፍልስፍና ማበርከት መቻሏን ማረጋገጫ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት ከውጭ የሚመጡ ርዕዮተ-ዓለሞችን (ካፒታሊዝም / ሶሻሊዝም) ስታስተናግድ የኖረችበትን የታሪክ ምዕራፍ በመቀየር የራሷን ሀገር በቀል ፍልስፍና ወደ ውጭ የምትልክ ሀገር ለመሆኗ ትልቅ ማሳያ እንደሆነም የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አመልክቷል፡፡

መጽሐፉ አፍሪካን፣ መካከለኛው ምስራቅን (በአረብኛ)፣ ደቡብ እስያን (በኡርዱ) እና አሁን ደግሞ ምስራቅ እስያን (በቻይንኛ) ተደራሽ ማድረጉ ፍልስፍናው ከተወለደበት የኢትዮጵያ ምድር ተሻግሮ አህጉራትንና የተለያዩ ባህሎችን የማስተሳሰርና የማቀራረብ ትልቅ የዲፕሎማሲ አቅም እንዳለውም ማሳያ ነው ።

Exit mobile version