አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2025/26 በጀት ዓመት 80 ቢሊየን ብር ትርፍ አገኘ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ የ2025/26 በጀት አፈጻጸምን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አቶ አቤ በመግለጫቸው ባንኩ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች 648 ቢሊየን ብር ብድር መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ 2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር መድረሱን ጠቁመው÷ በበጀት ዓመቱ 80 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር መገኘቱንና በዚህም አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ በ2 ዓመት 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን አስረድተዋል።
ባንኩ በቀጣዩ ዓመት 832 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ እንዲሁም ገቢውን 360 ቢሊየን ብር ለማድረስ ማቀዱን በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡
ከ6 ዓመት በፊት ባንኩ 90 በመቶ የሚሆነውን ብድር ለመንግሥት ተቋማት ያበድር እንደነበር አስታውሰው ÷ በበጀት ዓመቱ ግን 90 በመቶ የሚሆነው ወይም 588 ቢሊየን ብሩን ለግል ዘርፍ ማበደሩን አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይ ባንኩ 546 ቢሊየን ብር ብድር ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን÷ አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት አንጻር የ91 በመቶ እድገት አሳይቷል ነው ያሉት።
በዙፋን አምባቸው

