የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ታሪክ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረና ትልቅ መሠረት ያለው ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሀገሪቱ እየተከተለች ያለው ጎረቤት ተኮር እና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በርካታ ስትራቴጂካዊ ስኬቶችን አስመዝግቧል።
ኢትዮጵያ ሚዛናዊ፣ አጋርን ማብዛት ላይ ያተኮረ እና ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ የውጭ ግንኙነትን መርኋ በማድረግ ተሰሚነቷን እየጨመረች፤ ያላትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ በመጠቀም በቀጣናዊ ትስስር፣ በሰላምና ጸጥታ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚ ውህደት የዲፕሎማሲ ሚናዋን እያሳደገች ትገኛለች፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የምታደርገው ጥረት ትልቅ እውቅናን አትርፎላታል።
የውኃና የሃይል ድርድር ክርክሮችን ወደ ተጨባጭ የልማት ትስስሮች በመቀየር በቀጣናዊ መሠረተ ልማት ቅንጅት አህጉራዊ ተምሳሌትነቷን እያረጋገጠች ነው።
የዓባይ ግድብን ድርድር ከአፍሪካ አውድ ለማውጣት የተደረገውን ዓለም አቀፍ ጫና በማክሸፍ ወደ አፍሪካ ማዕቀፍ እንዲመለስ ማድረግ መቻሏም ትልቅ ድል ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና ወደ ሙሉ ስራ መግባት የቀጣናውን የሃይል ሚዛን የቀየረው ሲሆን፣ ሀገሪቱ ለጎረቤት ሀገራት በምታቀርበው የኤሌክትሪክ ሃይል የቀጣናውን የኢኮኖሚ ውህደት ይበልጥ አጠናክራዋለች፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስትራቴጂክ ጥምረቶች ውስጥ ያላት ተደራሽነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ይገኛል፡፡
ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የሌሎችም ተቋማት መስራችና አባል ሀገር ናት፡፡
አሁን ላይ የኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል መሆን በምስራቁ ዓለም ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ የአፍሪካን ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረክ ለማንጸባረቅ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
የአዲስ አበባ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት ሚናዋን መወጣት ደግሞ ሌላኛው ስኬት ነው፡፡
በሌላ መልኩ የሀገር ውስጥ የልማት ስኬቶችን ወደ ዲፕሎማሲያዊ አቅም በመቀየር ዓለም አቀፍ አድናቆትን ማትረፍ ተችሏል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርትና በምግብ ዋስትና ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ቅቡልነት ከፍ አድርጎታል።
ይህም የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤን በአዲስ አበባ እንድታስተናግድ መንገድ ከፍቷል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ሀገሪቱ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷ እና ለወደፊቱ የCOP ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለመቀበል ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየቷ ሌላው ድል ነው።
ኢትዮጵያ ያላትን አስተማማኝ የባህር በር እና የወደብ ተደራሽነት ፍላጎት በሰላማዊ፣ ህጋዊ እና በጋራ እድገት መርህ ላይ በተመሰረተ መንገድ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት ረገድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት ችላለች።
በጥቅሉ ሲታይ፣ ኢትዮጵያ የነበሩባትን የውጭና የውስጥ ጫናዎች በመቋቋም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የአካባቢ ጥበቃ ዲፕሎማሲዋን ከተረጂነት ወደ ስልታዊ አጋርነት ማሸጋገር ችላለች።
ይህ በአብሮ ማደግ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተው ስኬት አዲስ አበባ በቀጣናው ያላትን የዲፕሎማሲ መሪነት ቁመና ዳግም ያረጋገጠ ሆኗል።

