Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተፈጥሮ ጥብቅ ቦታዎችን በዲጂታል መጠበቅ የሚያስችል ድረ ገጽ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የተፈጥሮ ጥብቅ ቦታዎችን በዲጂታል መጠበቅ የሚያስችል ድረ ገጽ ይፋ አድርገዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ ስለሺ ግርማ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በቱሪዝም ዘርፉ ቴክኖሎጂ ነክ መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በማደራጀት ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያስገኙ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም በአብዛኛዎቹ የጥብቅ ቦታዎች የዱር እንስሳት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

ድረ ገጹ ጥብቅ ቦታዎችንና የእንስሳቱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እንዲሁም ቱሪስቶች በአካል ቦታው ድረስ ከመሄዳቸው በፊት ቀድመው መረጃዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ተገማች የቱሪስት እንቅስቃሴ እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ድረ ገጹ ባለስልጣኑ ያለውን ውስን የፓርክ ጠባቂዎችና የመስክ ባለሙያዎች የሰው ሃይል በቴክኖሎጂ በመደገፍ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመምራት ያግዛል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የዲጂታል ካርታዎችንና የጥብቅ ቦታ መረጃዎችን ለጎብኚዎች በማቅረብ የቱሪዝም መዳረሻዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version