አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከዲጂታል ስርዓትና የሰውሰራሽ አስተውሎት ጋር እየተሳሰረ የሚገኘው የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ነው አሉ።
2ኛው የአፍሪካ የህክምና ትምህርት ጉባኤ “የአፍሪካን የጤና ባለሙያ ኃይል ለአዳዲስ መጻኢ እድሎች እና ፈተናዎች ማዘጋጀት” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉባኤውን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጤና ባለሙያዎች ትምህርትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ተግባራት አከናውናለች፡፡
አዳዲስ የህክምና ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውንና ነባር ተቋማት እንዲጠናከሩ መደረጉን ገልጸው፥ ወጣት ኢትዮጵያውያን በጤና ሳይንስ ዘርፍ እንዲሰማሩ እድሎችን ለማሳደግ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡
ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር ሩዋንዳና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ከእህት የአፍሪካ ሀገራት ለመጡ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር የኢትዮጵያን የጤና ስርዓት ከሰው ሰራሽ አስተውሎትና ዲጂታል የፈጠራ አቅሞች ጋር በማስተሳሰር ጥራት ላለው የጤና አገልግሎት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
በጤና ኢንፎርማቲክስ፣ በዲጂታል ጤና፣ በሮቦቲክስና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ የጤና ምርመራ ላይ ትኩረት የሚያደርግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የኤአይ ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት እየተሰራ ያለውን ስራ አስረድተዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በጤናው ዘርፍ ፈጣን ለውጥ እያመጣ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እንደ አህጉር በዚህ ለውጥ ውስጥ ፈጣሪዎች፣ መሪዎችና አስፋፊዎች መሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ይህ ለውጥ ከዩኒቨርሲቲዎች መጀመር እንዳለበት ጠቁመው፥ በአካዳሚ፣ በኢንዱስትሪና በክሊኒካዊ ልምምድ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት፡፡
እነዚህ ሦስት ምሰሶዎች አብረው ሲሰሩ፣ ፈጠራ ከላቦራቶሪ ወደ ክፍል፣ ከክፍል ወደ ህሙማን አልጋ እንዲሁም ከህሙማን አልጋ ወደ እያንዳንዱ መንደርና አፍሪካዊ ከተማ ይደርሳል ሲሉ አስረድተዋል።
አፍሪካ ታይቶ በማይታወቅ ፈተናና እድል መገናኛ መንገድ ላይ መሆኗን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ሁሌም ለአህጉራዊ የጤና ዘርፍ ማደግ የማያወላውል ቁርጠኝነቷን በተግባር እያሳየች ትገኛለች ብለዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የ46 ሀገራት ተወካዮችና የጤናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ 750 ተሳታፊዎች እንዲሁም 117 የህክምና ትምህርትና ባለድርሻ ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በለይኩን ዓለም

