Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፍትሃዊና ጠንካራ የጤና ስርዓት ለመገንባት ከጤና ትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ለፍትሃዊና ጠንካራ የጤና ስርዓት ግንባታ ስኬት ከጤና ትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ።

2ኛው የአፍሪካ የህክምና ትምህርት ጉባኤ “የአፍሪካን የጤና ባለሙያ ኃይል ለአዳዲስ መጻኢ እድሎች እና ፈተናዎች ማዘጋጀት” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ ዲጂታል የጤና ስርዓትን ለማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርትን ለማሳደግ እንዲሁም ብቁና ለወደፊት የተዘጋጁ የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ ነው።

እንደ አህጉር በአግባቡ የሰለጠኑ፣ ብቁና ለወደፊት የተዘጋጁ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት ለአስተማማኝ የጤና ስርዓት መሰረት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በማስፋፋት፣ በጤና መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማትን በማጠናከር አስደናቂ ስኬቶችን አስመዝግባለች ብለዋል።

የጤና ዘርፉን ትርጉም ባለው መልኩ ለማሻሻል የጤና እንክብካቤን ማጠናከር፣ ዲጂታል ለውጥን ማፋጠን እንዲሁም ብቁ እና ለወደፊት የተዘጋጀ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት የሚሉ ቅድሚያዎች ላይ በመመስረት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም በጤና ዘርፍ ለውጥ ውስጥ ለሀገር ውስጥ ምርት ስትራቴጂያዊ ቅድሚያ መሰጠቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ ይህንን ለማሳካት ዘላቂ ፋይናንስ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዘላቂ የጤና ፋይናንስን አጠናክራ መቀጠሏን ጠቅሰው፥ በአሁኑ ወቅት ከ63 ሚሊየን በላይ ሰዎችን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

ከ47 በላይ የህዝብ ጤና ስልጠና ተቋማት መኖራቸውን ገልጸው፥ 22 ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የስፔሻሊቲና የሱፐር ስፔሻሊቲ ስልጠናዎችን በመስጠት በየዓመቱ 1ሺህ 200 ያህል ስፔሻሊስት ሐኪሞችን በማስመረቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም የድህረ ምረቃ የህክምና ትምህርትን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

በለይኩን ዓለም

Exit mobile version