አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሕዝቡ የሰጠን ባዶ ቼክ ነው፤ በታማኝነት ማገልገል የኛ ኃላፊነት ይሆናል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፥ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ጥልቅ አሳቢነትና ሰላም ፈላጊነት በግልጽ ያሳየበት ታሪካዊ መድረክ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ ምርጫውን ያካሄደው ለቀጣይ ትውልድ የጸናችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ በሚል ትልቅ ተስፋ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ሕዝቡ የሰጠን ባዶ ቼክ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ቼክ ላይ መልካም ስምን፣ ጠንካራ ሥራንና ስኬታማ ውጤትን መጻፍ የሁሉም አመራሮችና የፓርቲው የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የመረጠን የተጀመሩ የኢኮኖሚና የፀረ ሙስና ጥረቶችን በማጠናከር፣ የአገልግሎት አሰጣጥን አሻሽለን ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች ሀገር እንድናስረክብ የጣለብንን አደራ ለመወጣት ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻል፣ ሌብነትንና ሙስናን ለማጥፋት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለምንም ፍርሃት በነጻነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ድምፁን ሰጥቷል ብለው፤ ይህም በታማኝነትና ሕዝብን በክብር ማገልገል ምን ያህል ፍሬያማ እንደሆነ በተግባር ያሳየ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምርጫውን በሚመለከት ቀደም ባለው ጊዜ ባደረገው ውይይት 15 በመቶ ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመተዉ መወሰኑን ገልጸው፤ ይህ ዓይነቱ ውሳኔ በአፍሪካ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እጅግ አልፎ አልፎ የሚታይ የዴሞክራሲ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ብልጽግና ፓርቲ ካቀረባቸው አጀንዳዎች መካከል ግንባር ቀደሙ በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት መቆየት ያለበት ለ2 ዙር ብቻ ነው የሚል መሆኑን አንስተው፤ ይህ አቋም ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ መሠረት የሚጥል ታላቅ ታሪካዊ ርምጃ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጠዋል።
በአፍሪካ አብዛኛውን ጊዜ የሥልጣን ዘመንን የማራዘም ዝንባሌ እንጂ ዕድሜን የመገደብ ልምድ እንዳልነበረ አስታውሰው፤ ፓርቲያቸው ያቀረበው አጀንዳ በራሱ በየትኛውም የአፍሪካ ሀገር የማይታይ መሆኑን አብራርተዋል።
ዘንድሮ የተካሄደው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የሕዝብ ይሁንታ በግልጽ የታየበት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በሶስና አለማየሁ

