Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በትምህርት ዘርፍ ላይ የምንሰራው ስራ ከየትኛውም በላይ የምንኮራበት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በትምህርት መስክ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ከየትኛውም ዘርፍ በላይ የሚያኮሩ ናቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህን የተናገሩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት 35 ሺህ መዋዕለ ህጻናትን በመላው ሀገሪቱ መገንባት መቻሉን አንስተው፤ እነዚህ ህጻናት ከ20 ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ህልውና እንደሚሆኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት 35 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሰራታቸውንም አንስተዋል።

በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስፋት እየተገነቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከ30 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ በሁሉም ክልሎች ሞዴል ትምህርት ቤቶች በመሰራት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ከታች ጀምሮ በትኩረት ለመስራት በማቀድ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተው፤ በሀገር ደረጃም ሆነ በአፍሪካ በጥራቱ ግንባር ቀደም የሆነ ዩኒቨርሲቲ በመገንባት ላይ እንደሆነም ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ፖሊሲው የብልጽግና ፓርቲ ቢሆንም፤ የኢዜማ ፓርቲ አባል ሆነው ለፖሊሲው መሳካት በታማኝነት በማስፈጸም ውጤት ላመጡት የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመልካም ፍቃዱ

Exit mobile version