Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመደመር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታ በቅርቡ ይጠናቀቃል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታ በጥቂት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፥ በትምህርት ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለል የቆየውን የጥራት ችግር ከመሠረቱ ለመፍታትና ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

መንግሥት ለታችኛው የትምህርት መሠረት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው፤ እየተሰሩ ያሉ መዋዕለ ሕጻናት ከ15 እና 20 ዓመታት በኋላ የሀገር ሕልውና፣ የሳይንስና የዕድገት መሠረት የሚሆኑ ሀገር ተረካቢዎችን ያፈራሉ ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ፣ ዳያስፖራውና ባለሀብቶች የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ድጋፍ በማድረግ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ ልዩ ልዩ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

በግጭቶች ምክንያት የፈረሱና የተዘረፉ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመጠገንና ወደ መደበኛ የማስተማር ሥራ ለማስገባት በስፋት መሰራቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በተዘረጋው አዲስ የብሔራዊ ፈተና ሥርዓትና ጥብቅ ቁጥጥር በተማሪዎች፣ በወላጆችና በትምህርት ቤቶች ዘንድ ኮርጆ ማለፍንና ስርቆትን የመጸየፍ በጎ ባህል እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በትምህርት ዘርፍ እየተከናወኑ ባሉ ስትራቴጂካዊና ትውልድ ተኮር ሥራዎች በከፍተኛ ደረጃ አኩሪ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው፤ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የታችኛው የትምህርት መሠረትና የጥራት ደረጃ በአግባቡ ሳይጠናከር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ቁጥር ማብዛት ስለማይገባ ባለፉት ሰባት ዓመታት አዳዲስ መደበኛ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳልተገነቡ ተናግረዋል።

ሆኖም ግን የሰው ሠራሽ አስተውሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የዓለም የወደፊት የዕድገት ዕጣ ፈንታ መሆኑን መንግሥት ቀድሞ በመገንዘብ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ላይ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም በመላው አፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ዘመናዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታ በጥራት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው በጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version