አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኮንትሮባንድ እና ንግድ ማጭበርበር ሀገር ልታጣ የነበረውን 380 ቢሊየን ብር ማዳን ተችሏል አለ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ በዓመቱ በገቢ አሰባሰብ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በኮንትሮባንድ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል።
በዚህም መሰረት በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ ዕቃዎች ቀረጥ ከ738 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥ፣ ኮንትሮባንድ እና የንግድ ማጭበርበርን ለመከላከል እና አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ ኮሚሽኑ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማልማት ገቢራዊ ማድረጉን አስገንዝበዋል፡፡
ጊዜውን የዋጀ ፣ ከዓለም ዓቀፍ የንግድ አሰራር ጋር የተጣጣሙ የሕግ ማዕቀፎችን የመቅረጽ እና የማሻሻል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በኮንትሮባንድ እና ንግድ ማጭበርበር ሀገር ልታጣ የነበረውን 380 ቢሊየን ብር ማዳን መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል 28 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በኮንትሮባንድ ከተያዙት መካከል የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ መድኃኒቶች፣ አልባሳት፣ አደንዛዥ ዕጾች፣ ማዕድናት እና የቁም እንስሳት ይገኙበታል፡፡
ለተመዘገበው ስኬት ተቋማዊ ሪፎርም፣ በቴክኖሎጂ ራስን ማዘመንና የሰው ኃይል ልማት ላይ የተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስገንዝበዋል፡፡
በዙፋን አምባቸው

