አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ገንዘብ ዝውውርን የሁለንተናዊ ብልጽግናዋ ወሳኝ ምሰሶ አድርጋ እየተከተለች ትገኛለች።
አስደናቂ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምዕራፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በጥሬ ገንዘብ ላይ ከተመሰረተ አሰራር ወጥታ በዲጂታል ምህዳር በየዓመቱ በትሪሊየን የሚቆጠር የገንዘብ ዝውውር ወደሚከናወንባት ሀገር ተቀይራለች።
የመሰረተ ልማት መስፋፋትና የቴሌኮም ዘርፉ ማደግ ደግሞ ለተመዘገበው አስደናቂ ለውጥ ግንባር ቀደም ኃይል ነው፡፡
የሀገሪቱ የቴሌኮም ተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 87 ነጥብ 9 ሚሊየን በማደጉ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ 99 ነጥብ 8 በመቶ የሕዝብ ተደራሽነትን እንዲያገኝ አስችሎታል።
ከዚህም በላይ የ4ጂ እና የ5ጂ መስፋፋት ለዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ መፋጠን አስተማማኝ መሰረት ጥሏል።
በዚህ የዲጂታል ምህዳር ውስጥ የላቀ ስኬት ያስመዘገበው የኢትዮ ቴሌኮም ‘ቴሌብር’ መተግበሪያ በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር 58 ሚሊየን አድርሷል፡፡
ቴሌብር ብቻውን ከ58 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን በማፍራት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ ከ6 ነጥብ 88 ትሪሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር አስተናግዷል፡፡
ይህ መተግበሪያ ከገንዘብ ማስተላለፍ ባለፈ ለዜጎች የብድር አገልግሎት በመስጠት ለፋይናንስ አካታችነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
በሞባይል የሚደረገው የገንዘብ ዝውውር በጥሬ ገንዘብ ከሚደረገው መብለጡ የሽግግሩን ጥልቀት ያሳያል።
ይህ የፋይናንስ ዘርፍ ዘመናዊነት የግብይት ወጪን በመቀነስና ለዜጎች ምቾትን በመፍጠር ብቻ የሚገደብ ሳይሆን የፋይናንስ ደህንነትንና ግልጽነትን በማረጋገጥ ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የፋይናንስ ተቋማትን አሰራር በማዘመንና ዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓቶችን በመዘርጋት፤ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና በማጭበርበር ወንጀል ሊመዘበር የነበረ በቢሊየን የሚቆጠር ሃብት ማዳን ተችሏል።
እንዲሁም የወንጀል ተጠርጣሪዎች የሚንቀሳቀሱባቸው የባንክ ሂሳቦች እንዲታገዱ በማድረግ ደኅንነቱ የተጠበቀ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ትልቅ አቅም ሆኗል።
አጠቃላይ የዲጂታል ሽግግሩ አሁን ላይ ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ባለፈ ወደ ተጨባጭ ድርጊትና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወደሚመራ አስተዳደር እየተሸጋገረ ነው፡፡
የፋይዳ መታወቂያ ደግሞ ለዜጎች ቀልጣፋ አሰራርን በማበርከት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።
መንግሥት እየተገበረ የሚገኘው የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ የተጀመረውን ስኬት ይበልጥ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ይህ የዲጂታል ክፍያና የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ዘመናዊነት ሀገሪቱ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በቱሪዝም እና በሌሎችም ቁልፍ የልማት መስኮች ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ የማይናወጥና አስተማማኝ የፋይናንስ የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል።
በዮናስ ጌትነት

