Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ግንባር ቀደም ማሳያ ነው – የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ግንባር ቀደም ማሳያ ነው አሉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት÷ ኢትዮጵያ የምታካሂደው የአረንጓዴ ዐሻራ ፖሊሲና የችግኝ ተከላ ሒደት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

የአየር ንብረት ጉዳይ መላውን ዓለም የሚያሳስብ ዓለም አቀፋዊ ክስተት በመሆኑ ኢትዮጵያ ይህንን ሒደት በተለይም ከአፍሪካ አህጉር በግንባር ቀደምትነት እየመራችው እንደምትገኝ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የስሪላንካ አምባሳደር ኒርማላ ፓራናቪታ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱን የአረንጓዴ ልማት መርሐ ግብር መተግበሯ እጅግ ብልህነት የተሞላበት አካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አበርክቶ ያለው መሆኑን ጠቁመው÷ ስሪላንካ በዚህ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት ለመሥራት ያላትን ፍላጎት ተግባራዊ የምታደርግበትን መንገድ እያጠናች መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፓኪስታን የንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ተወካይ ባሲት ሳሊም ሻህ ÷ የአረንጓዴ ዐሻራ ለኢትዮጵያ የተለየ ውበትና መስህብ ከመለገሱ በላይ ከአየር ብክለት የጸዳ አካባቢን ለማስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዚህ ከፍተኛ ደረጃ መብቃት መቻላቸው ሊደነቅ የሚገባው ተግባር ሲሉም አውስተዋል፡፡

Exit mobile version