Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሳይበር ደህንነትን የሚያስጠብቅ የቴክኖሎጂ አቅም ተገንብቷል – አስተዳደሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል የሕግ፣ የአሰራርና የቴክኖሎጂ አቅም ገንብታለች አለ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር።

ከትናንት ሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፉ የፓርላማ የመረጃ ደኅንነት ፎረም ተጠናቅቋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ጉታ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሳይበር ደህንነት ስጋት ድንበር የለሽ በመሆኑ ስጋቶችን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ሕጎችን የማጣጣምና የቅንጅት ስራ ወሳኝ ነው።

ሀገራት የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅና የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመከላከል ተናባቢ ሕጎች ሊኖራቸው እንደሚገባ አንስተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በዚህ አግባብ በመስራት የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል የሕግ፣ አሰራርና ቴክኖሎጂ አቅምን ገንብታለች ብለዋል።

ፎረሙ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መድረኮችን ለማዘጋጀት ያላትን አቅም ለማሳየትና ለገጽታ ግንባታ አስተዋፅዖ የሚያበረክት መሆኑን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በፎረሙ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም፣ የሳይበር ደኅንነት፣ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና መሰል ዓለም አቀፍ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።

Exit mobile version