Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሜጋ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር እናሳያለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጀመርናቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት አጠናቅቀን ለምርቃት ለማብቃት ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየን እንቀጥላለን አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብረ ማርቆስ ከተማ ለ30 ዓመታት ያህል ተቋርጦ የነበረውን የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የአውሮፕላን ማረፊያ በዛሬው ዕለት በይፋ መርቀዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው የደብረ ማርቆስና የአካባቢው ሕዝብ ለዓመታት በጉጉት ሲጠብቀው ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥በዘመናዊ መልክ ተሻሽሎና ደረጃው ከፍ ብሎ ተገንብቶ ዛሬ በይፋ መመረቁን ገልጸዋል፡፡
ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር፤ የሕዝባችንን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስና የጀመርናቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት አጠናቅቀን ለምርቃት ለማብቃት ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየን ነው ያሉት፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው ሥራ መጀመሩ የአካባቢውን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ በማነቃቃት ለአካባቢውና ለመላው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት አመልክተዋል፡፡
በ2ሺህ 400 ሜትር ርዝመት እና 30 ሜትር ስፋት ላይ የተገነባው አውሮፕላን ማረፊያው እንደ Q400 እና B737 ያሉ ግዙፍ የሕዝብና የጭነት አውሮፕላኖችን ማሳረፍ የሚያስችል ከፍተኛ ዐቅም መፍጠሩንም አስረድተዋል።
Exit mobile version