አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እኛና ከእኛ በፊት የነበሩ ሰዎች ያላሳኳቸውን ጉዳዮች ልጆቻችን ዳግም እንዳያጡ በታላቅ ሃላፊነት መስራት ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የምክክር ጉባዔ በቀላሉ የማይደገም፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ በወሰደው ጊዜና በስፋቱ በእጅጉ የገዘፈ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ በብዙ ምሳሌ የሚሆን የውይይት፣ የምክክር፣ የንግግር እና ሁሉን አቀፍ መድረክ መሆኑንም ነው ያወሱት፡፡
የምክክር ጉባዔው ልባም ለሆኑ ሰዎች የታሪክ የአጋጣሚን እንዲሁም የዕድልን ጠቃሚነት ማዝለቅ ለፈለጉ ሰዎች በብዕሩ ሀገርን ለዘመናት የሚገነባ ታሪክ ለመጻፍ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
በተቃራኒው ይህን ለማይጠቀሙ ደግሞ ታሪክ ብራናና ብዕር ቢያቀብላቸው ሀገርን ከሚጠቅም ይልቅ የሚጎዳ፣ ከሚገነባ ይልቅ የሚያፈርስ፣ ከሚያበለጽግ ይልቅ የሚያደኸይ፣ ከሚያሰፋ ይልቅ የሚያጠብ ታሪክ ጽፈው ያልፋሉ ነው ያሉት፡፡
መሰል ታሪክ ዛሬ በእኛ እንዳይደገም ከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት ተሰምቶን በታላቅ አክብሮት ልንከውነው ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
እኛ እና ከእኛ በፊት የነበሩ ሰዎች ሊያሳኳቸው ሲገባ ያላሳኳቸው ጉዳዮችን ልጆቻችን ዳግም እንዳያጡ በታላቅ ሃላፊነት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

